ለዘጠኝ ዓመታት የተጓተተው የካፍ አካዳሚ ተጨማሪ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ ተመደበለት

የካቲት 2፣ 2009

ግንባታው ሲካሄድ የቆየውና መጠናቀቅ ካለበት ጊዜ በዘጠኝ ዓመት የዘገየው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (የካፍ) አካዳሚ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ተመደበለት።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሰሚት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የካፍ አካዳሚ ግንባታው የተጀመረው በ1997 ዓ.ም ሲሆን፤ በእቅዱ መሰረት በሶስት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቅ ነበር።

ይሁን እንጂ አካዳሚው በክትትል ማነስ ግንባታው እስከአሁን በመጓተት ላይ ነው።

ስራው ሲጀመር ካፍ የግንባታው ስራ ለግብፃውያን ተቋራጮች የሰጠ ቢሆንም፤ በተለያዩ  ምክያቶች ግንባታውን በማዘግየታቸውና በተፈለገው ጥራት ደረጃ ባለመስራታቸው ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል። ከዚህ በኋላም ከአራት ዓመት በፊት ለኢትዮጵያውያን ተቋራጮች እንዲሰጥ ተደርጓል።

ኢትዮጵያውያን ተቋራጮች የጀመሯቸውን ህንጻዎች ያጠናቀቁ ቢሆንም የእግር ኳስ ሜዳው ግን "የውሃ ችግር ገጥሞናል" በሚል ምክንያት  ውላቸውን አቋርጠዋል።

አካዳሚው እስካሁን በነበሩት 12 ዓመታት የስፖርተኞች የመኝታ ክፍሎች፣ የስልጠና ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መጠናቀቅ ችለዋል።

ይሁን እንጂ  በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ ሳር ለመስራት የታሰቡት ሁለት የእግር ኳስ ሜዳዎች ገና በጅምር ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ እየተገነባ ካለው የካፋ አካዳሚ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ የተጀመረው የካሜሮን አካዳሚ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ከገባ ከሁለት ዓመት በላይ አስቆጥሯል።

የካሜሮን አካዳሚ ሶስት የእግር ኳስ ሜዳ፣ የሥልጠና አዳራሽና የመኝታ ክፍሎች፣ ከጂምና መዋኛ ገንዳ በተጨማሪ ሳውና፣ ስቲም ጃኩዚ ሌሎች መሰል ነገሮችን ያሟላ ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ እንደገለጹት፤ አካዳሚው የዘገየው በካፍ ኃላፊዎችና እና በኢትዮጵያ የካፍ ተወካይ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ የክትትል ማነስ የተፈጠረ ችግር እንደሆነ ነው የተናገሩት።

''አካዳሚው ከመዘግየቱም በተጨማሪ  የጥራት ችግር አለበት፤ ይህንም በካፍ በኩል የተማመንበት ነው'' ብለዋል።

አቶ ወንድምኩን እንደተናገሩት፤ በቀጣይ ይህን ለማስተካከልና ተጨማሪ  የውሃ መዋኛ ገንዳ፣ ጂምና ሌሎች ማዘውተሪያ ቦታዎች አካቶ ለመስራት በካፍ በኩል በጀት ተመድቧል።

ለዚህም በካፍ በኩል ከአራት ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለታል።

በኢትዮጵያ የካፍ ተወካይ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ከዚህ በፊት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ግንባታው የዘገየው በግብጻውያን ተቋራጮች ችግር ምክንያት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵውያን ተቋራጮች በኩል ደግሞ በአካባቢው በነበረው የውሃ ችግር ምክንያት የእግር ኳስ ሜዳውን ሳይሰሩ ውላቸውን ማቋረጣቸውን ነው የተናገሩት።

ከዚህ በፊት "ምን ያህል ገንዘብ ወጪ ተደርጎበታል?" ላልናቸው ጥያቄ በካፍ ተወካይ በአቶ ሳህሉም ሆነ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በኩል የሚያቁት ነገር እንደሌለ ነው የተገለጸው።

ወጪው ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም ሙሉ በሙሉ በካፍ የሚሸፈን መሆኑ ይታወቃል፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም የመሬት አቅርቦትና ለግንባታው የሚውሉ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ድጋፍ አድርጓል።

ካፍ በኢትዮጵያ እያስገነባው ያለው የስፖርት አካዳሚ ሲጠናቀቅ በዋናነት በመካከለኛውና ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ውድድሮች ይደርጉበታል ተብሎ ይታመናል። እንዲሁም "የስፖርተኞች የዳኞችና የስፖርት አስተዳደር ስልጠና እና  ማደሪያ ይሆናል" ተብሎ ይጠበቃል።

ምንጭ፡- ኢዜአ

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች