ዋልያዎቹ ከ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ውጭ ሆኑ

ህዳር 3፣2010

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአውሮፓውያኑ 2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ መልስ  ከሩዋንዳ አቻው ጋር ዛሬ በኪጋሊ ብሔራዊ ስታዲየም አድርጎ  0-0 በሆነ ውጤት አጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ብሔራዊ ቡድኑ ከ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ውጭ ሆኗል።

ብሔራዊ ቡድኑ ሞሮኮ በምታስተናግደው የቻን ውድድር ለመሳተፍ ከሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ 3ለ2 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ በድምር ውጤት 3ለ2 በመሸነፍ ከውድድር ውጭ ሆኗል።

ዋልያዎቹ  በሱዳን ብሔራዊ ቡድን ተሸንፈው ከ2018ቱ የቻን ውድድር ውጪ ሆነው እንደነበር ይታወሳል።  ሆኖም ግብፅ በአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  በውድድሩ እንድትሳተፍ የቀረበላትን ጥያቄ አለመቀበሏን ተከትሎ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ የማጣሪያ ጨዋታ አድርገው አሸናፊው ሞሮኮ በ2018 ለምታስተናግደው የቻን ውድድር እንዲሳተፍ ካፍ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

የአገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የ2018 የቻን አፍሪካ ዋንጫ 16 አገሮች የሚካፈሉበት ሲሆን የዘንድሮው ውድድር ለ5ኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው።

 

 

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች