ሙክታር እድሪስ በትሬንቶ በተካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር አሸነፈ

መስከረም 21፣2010

የጂሮ አል ሳስ በሚል ስያሜ በሚታወቀውና ዘንድሮ ለ71ኛ ጊዜ በጣሊያን ትሬንቶ ከተማ  የተከናወነው  የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር  አትሌት ሙክታር እድሪስ  አሸንፏል፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሶስት ተከታትለው በገቡበት የጎዳና ላይ 10 ኪ.ሜ. ውድድር  ሙክታር  እድሪስ 28 ደቂቃ ከ54 በሆነ ሰአት በመግባት ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቋል፡፡

ሌላው ኢትዮጵያዊው ጥላሁን ሀይሌ በ28 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ያሲን ሀጂ 29 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ ሰአት በመግባት ውድድሩን ሶስተኛ በመሆን ጨርሷል፡፡

በዚህ ውድድር ላይ ዘንድሮ በተከታታይ ሶስተኛ ድሉን የተቀዳጀው ሙክታር ከውድድሩ በኋላ ለውድድሩ አዘጋጆች በሰጠው አስተያየት ‹‹በከፍተኛ ቦታዎች  ላይ መለማመዴ ለውጤታማነቴ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል ብሏል፡፡

በዓለም ሻምፒዮና ላይ አሸናፊ መሆን ተጠባቂነትን ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ ልምምዴን ይበልጥ አጠናክሬ መስራቴን መቀጠል ይኖርብኛልም ብሏል፡፡

በትሬንቶ በተከታታይ ለሶስተኛ ዓመት ማሸነፍ መቻሌ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ወደዚህ በመጣሁ ቁጥር ሁሉም ሰው አሸናፊ እንደምሆን ይጠብቃል፡፡ በውድድሩ መሀል ድካም በተሰማኝ ጊዜ በማያቋርጥ የሞራል ድጋፋቸው ለአሸናፊነት እንድበቃ እገዛ ያደረጉልኝን የትሬንቶ ደጋፊዎች ላመሰግናቸው እወዳለሁ›› ብሏል፡፡

አትሌት ሙክታር የለንደን ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንግሊዛዊውን ሞሃመድ ፋራህን በማስከተል የ5 ሺህ ሜትር አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።

የጂሮ አል ሳስ ዓለም አቀፍ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ለወንድ አትሌቶች ብቻ የሚዘጋጅ ውድድር ነው።

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች