ሴኔጋል ለዓለም ዋንጫ ማለፏን ስታረጋግጥ የሞሮኮና ኮትዲቯር ጨዋታ ተጠባቂ ሆኗል

ህዳር 02፤2010

ሴኔጋል ደቡብ አፍሪካን 2ለ0 በማሸነፍ ከ16 ዓመታት በኋላ ሩሲያ በምታዘጋጀው የዓልም ዋንጫ ማለፋቸውን አረጋግጣለች፡፡

የማሸነፊያ ግቦቹንም ዲያፍራ ሳክሆ በ12ኛው ደቂቃና የደቡብ አፍሪካው ተከላካይ ታማሳንካ ኢምኪዜ በ38ኛው ደቂቃ ላይ በራሱ ላይ በማግባት ነው፡፡

በጨዋታው የሴኔጋልና የሊቨርፑሉ የፊት እጥቂ ሰይዱ ማኔ ኮኮብ ሆኖ ውሏል፡፡

በዚህም ግብጽና ናይጄሪያን በመከተል ከአፍሪካ ለ2018ቱ የዓለም ዋንፃ ያለፈች ሶስተኛ ሃገር ሆናለች፡፡

ቀሪዎቹ ሁለት ሃገራት ለዓለም ዋንጫው ለማለፍ የሚያደርጉት ፍክክር ይጠበቃል፡፡

ከምድብ አንድ ቱኒዚያ ከሊቢያና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከጊኒ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ ነው፡፡

ቱኒዚያ ምድቡን በ13 ነጥብ የምትመራ ሲሆን አንድ ነጥብ ማግኘት የሩሲያውን ትኬት እንድቶቆርጥ ያደርጋታል፡፡

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ ጊኒን በሶስት ጎልና ከዚያ በላይ ማሸነፍ የሚጠበቅባት ሲሆን ያላት ነጥብም 10 ነው፡፡

ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ ደግሞ ኮትዲቯር ከሞሮኮ የሚያደርጉት ጨዋታ ሲሆን ሞሮኮ ምድቡን በዘጠኝ ነጥብ ስትመራ ኮትዲቯር ደግሞ በስምንት ትከተላለች፡፡

ሞሮኮ አንድ ነጥብ ብቻ የሚያስፈልጋት ሲሆን ኮትዲቯር ማሸነፍ ግዴታ ይሆንባታል፡፡

ሁለቱም ጨዋታዎች ዛሬ የሚካሄዱ ይሆናል፡፡

እስካሁን ለ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ አህጉር 118 ጨዋታዎች የተካሄዱ ሲሆን 294 ግቦ ከመረብ አርፈዋል፡፡

ይህም ሲሰላ በአንድ ጨዋታ 2.5 ግብ ተቆጥሯል ማለት ነው፡፡

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች