ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊጉ በግብ ተንበሸበሸ

ጥቅምት 08፣2010

በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ሶስተኛ መርሃግብር ጨዋታዎች ሊቨርፑል ማሪቦርን 7ለ0 በመርታት የምድብ መሪነቱን ተቆናጧል፡፡

ከምድብ አምስት እስከ ስምንት በተካሄዱ 8 ጨዋታዎች ተጠባቂው የሪያል ማድሪድ እና ቶተንሃም ጨዋታም በ1 አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ሊቨርፑል ከግማሽ ደርዘን በላይ ባስቆጠረበት ጨዋታ ፍርሚኖዮ እና ሳላህ ሁለት፣ ሁለት ግብ ሲያስቆጥሩ፤ ቻምበርሊን አርኖርድ እና ኩቲኒዮ ቀሪዎችን ግቦች ከመረብ አገናኝተዋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ሊቨርፑል ምድብ አምስትን ከስፓርታክ ሞስኮ ጋር በእኩል 5 ነጥብ መምራት ችሏል፡፡ ስፓርታክ ሞስኮ በምሽቱ ጨዋታ ሲቪያን 5ለ1 ረቷል፡፡

በምድብ ስምንት በበርናባው ስታዲዮም ቶተንሃምን ያስተናገደው ሪያል ማድሪድ ጨዋታውን በ1 አቻ አጠናቋል፡፡ ግቡን ለቶተንሃም ከሀሪኬን የተጨረፈችውን ኳስ ቫራል በራሱ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡

ለማድሪድ ደግሞ ሮናልዶ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡ ምድቡን ቶተንሃም በእኩል 7 ነጥብ እና 5 ግብ ከሪያል ማድሪድ ጋር ይመራል፡፡

በሜዳው ናፖሊን በስተርሊንግ እና ናቫስ ግቦች 2ለ1 የረታው ማንችስተር ሲቲ ምድብ ስድስትን በ3 ነጥብ ልዩነት እንዲመራ አስችሎታል፡፡

ሻምፒዮንስ ሊጉ ዛሬም ቀጥሎ ሲካሄድ ቤኔፊካ ከማንችስተር ዩናይትድ፣ ቸልሲ ከሮማ 3፡45 የሚያደርጉት ጨዋታ ከቡድኖች ተፎካካሪነት አንፃር  ተጠባቂ ነው፡፡ ቀሪ ስድስት ጨዋታዎችም የዕለቱ መርሃግብሮች ናቸው፡፡

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች