አትሌት ፍሰሀ አበበ ከዚህ አለም በሞት ተለየ

መስከረም 25፣2010

በ11ኛው የአለም አገር አቋራጭ ሻምፕዮና ላይ ተሳትፎ ለአገሩ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘው አትሌት ፍሰሀ አበበ ከዚህ አለም በሞት ተለየ።

በቀድሞ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ጊዶ ወረዳ ልዩ ስሙ ለባ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ የተወለደው ፍሰሀ አበበ ወልደማርያም የሩጫውን አለም የተቀላቀለው ሀዋሳ ከተማ የካምቦኒ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ ሲሆን ከ200 ሜትር ጀምሮ ባሉ የአጭር ርቀት የሩጫ ተግባራት ላይ  ውጤታማ ተሳትፎ ነበረው።

አትሌት ፍሰሀ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር መጋቢት 20/1983 በብሪታንያ ጌትቬድ ከተማ በተዘጋጀው 11ኛው አገር አቋራጭ ሻምፕዮና ላይ ተሳትፎ ለአገሩ የወርቅ ሜዳልያ አስገኝቷል።

በኒውዮርክ ከተማ በተካሄደው 12ኛው የአለም አገር አቋራጭ ሻምፕዮና ላይም አገሩን ወክሎ ተሳትፏል።

አትሌቱ  በአገር ውስጥ ውድድሮችም ውጤታማ መሆን የቻለና ስመ ጥር አትሌት እነበረ።

አትሌት ፍሰሀ  አበበ መስከረም 23/2010 ዓ.ም ሌሊት ላይ በድንገት ማለፉን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለኢቢሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች