የዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ መርሃ ግብርና የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ውጤት

ነሃሴ 19፤2009

የ2017 የዳይመንድ ሊግ መርሃ ግብር ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት ብቻ የሚቀረው ሲሆን በተለይም አፍሪካዊያን አትሌቶች ውጤታማ ሊሆኑባቸው ርቀቶች አጠቃላይ ውጤት እና የትላንቱን ውጤት እንመልከት፡፡

ትላንት በዙሪክ ተካሄዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ሙክታር እድሪስ እና ዮሚፍ ቃጄልቻ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ ደግሞ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ሞ ፋራህ ውድድሩን 13፡06.05 በሆነ ሰዓት ሲያጠናቅቅ ሙክታር እድሪስ ደግሞ 13፡06.09 ሰዓት ሁለተኛ ሲሆን እንዲሁም ዮሚፍ ቃጄልቻ 13፡06.18 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ሰለሞን ባረጋ አራተኛ እንዲሁም የኔው አላምረው ስድስተኛ እና ብርሃኑ ለገሰ ዘጠነኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

በወንዶች 1500 ሜትር ደግሞ ኬንያዊያኑ ማንንም ጣልቃ ሳያስገቡ ከአንደኛ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው በማጠናቀቅ በርቀቱ የበላይነታቸውን አሳይተዋል፡፡

ቲሞቲ ቼሪዩት 3፡33.93፤ ሲላስ ኪፕላጋት 3፡34.26 እንዲሁም ደግሞ ኤሊጃህ ሞቴኒ ማናንጎይ 3፡34.65 በሆነ ሰዓት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

በወንዶች 100 ሜትር ውድድር ደግሞ እንግሊዛዊው ቺጅንዱ ኡጃህ አሸናፊ በመሆን ተመልካቹን ያስደመመ ሲሆን የለንደኑ የአለም ሻምፕዮናው ጀስቲን ጋትሊን አራተኛ ወጥቷል፡፡

በሴቶቹ 3000 ሜትር መሰናክል ደግሞ ባህሬናዊቷ ሩት ጃቤት ቀዳሚ ስትሆን ኬንያውያኑ ቢትሪስ ቾብኮዬት እና ኖራህ ጁሬቶ ናሩህ ሁለተኛ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ሲያጠናቅቁ ኢትዮጵያውያኑ ሶፊያ አሰፋና እቴነሽ ዲሮ 7ኛ እና 9ኛ ሆነው ውድድሩን አጠናቀዋል፡፡

በሴቶቹ 800 ሜትር ሩጫ እንዲሁ ካስተር ሰማኒያ አሸናፊ ስትሆን ቡሩንዳዊቷ ፍራንሲስ ኒዮንሳባ ሁለተኛ፤ ኬንያዊቷ ማርጋሬት ኒያይሬራ ሶስተኛ እንዲሁም ኢትዮጵያዊቷ ሃብታም አለሙ አራተኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን ጨርሰዋል፡፡

አጠቃላይ የየርቀቱን የደረጃ ሰንጠረዥ ስንመለከት በ100 ሜትር ወንዶች ካናዳዊው አንድሬ ዴግራሴ አንደኛ ሆኖ ሲመራ፤ ኮትድቯራዊው ቤን ዩሱፍ እና ደቡብ አፍሪካዊው አካኒ ሲምቢኔ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡

በሴተቹ ደግሞ ጃማይካዊቷ ኤሊየኔ ቶምፕሰን፤ ኮትዲቯራዊቷ ማሪ ጀሴ ታሉ እንዲሁም ናይጄራዊቷ ብሌሲንግ ኦካግባሬ ኢግሆቴጉኖር ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለው ደረጃ ይዘዋል፡፡

በ400 ሜትር ወንዶች ደግሞ ቦትስዋናዊው ባቦሎኪ ታቤ ቀዳሚ ደረጃን ተቆናጧል፡፡

በወንዶቹ 800 ሜትር ደግሞ ቦትስዋናዊው ኒጄል አሞስ ሰንጠረዡን እየመራ ሲሆን ኬንያዊው ኪፕዬጎን ቤት ሁለተኛ ደረጃን ይዟል፡፡

በሴቶቹ 800 ደግሞ ቡሩንዳዊቷ ፍራንሲስ ኒዮንሳባ፤ ደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሰማኒያ እንዲሁም ኬንያዊቷ ማርጋሬት ዋምቡይ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለው ደረጃ ይዘዋል፡፡

በወንዶቹ 1500 ሜትር እንዲሁ ኬንያዊያኑ ኤሊጃህ ሞቴኒ ማናንጎይ እና ቲሞቲ ቼሪዩት አንደኛ እና ሁለተኛ ሲሆን ኢትዮጵያዊው አማን ዎቴ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡

በሴቶቹ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ጉዳፍ ጸጋይ 6ኛ፤ ዳዊት ስዩም 7ኛ እንዲሁም በሱ ሳዶ 10ኛ ደረጃን ይዘው የሽልማቱ ተቋዳሽ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

በወንዶቹ 5000 ሜትር ደግሞ ኢትዮጵያዊያኑ ዮሚፍ ቃጄልቻ እና ሙክታር እድሪስ በእኩል 19 ነጥቦች አንደኛ እና ሁለተኛ ሲሆኑ ኬንያዊው ጆሹዋ ኪፕሩይ ቼፕቴጊ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡

በሴቶቹ 5000 ደግሞ ኬንያዊያኑ ሄለን ኦሳንዶ ኦቢሪና ማርጋሬት ቼሊሞ ኪፕኬምቦይ አንደኛ እና ሁለተኛ ሲሆኑ ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግዴይ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡

የዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ መርሃ ግብር ሊጠናቀቅ ሳምንት በቤልጂዬም ብራስል የሚደረገው ውድድር ብቻ ይቀረዋል፡፡

በአብዛኞቹ የውድድር አይነቶች ላይ ያለው የደረጃ ሰንጠረዥ በብራስልሱ ውጤት ሊቀያየር የሚችል ሲሆን በተለይም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከፍተኛ የሽልማት ደረጃ ውስጥ ሊካተቱበት የሚችሉት ርቀቶች እንመልከት፡፡

በወንዶች 1500 ሜትር አማን ዎቴ፤ ዮሚፍ ቃጄልቻ እና ሙክታር እድሪስ በወንዶች 5000 ሜትር፤ በሴቶች 1500 ሜትር ለተሰንበት ግዴይ፤  በሴቶች 5000 ሜትር ሶፊያ አሰፋ ናቸው፡፡

ይህንንም ስንመለከት በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያኑ እያስመዘገቡት ያለው ውጤት ከኬኒያዊያን አንጻር ሲታይ እጅጉን አነስተኛ መሆኑን መረዳት የሚቻለው፡፡

በዚህ ውድድር ቢያንስ ከ10 በላይ የሚሆኑ ኬንያዊያን አትሌቶች ከፍተኛ የሽልማት ደረጃ ውስጥ መግባት የሚችሉበትን ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡

ምንጭ፡ አይደብልኤፍ

 

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች