የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው በክብረወሰን ተጀመረ

ግንቦት 08፣2009

46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ስታዲዮም ሲጀመር አዲስ ክበረ ወሰን በሱሉስ ዝላይ ወንዶች ተመዝግቧል፡፡

በውድድሩ ሁሉም ክልሎች እና 30 ክለቦች የተሳተፉ ሲሆን 1ሺህ 265 አትሌቶች ይካፈላሉ፡፡

በሻምፒዮናው መጀመሪያ ሶስት የፍፃሜ ውድድሮች ተካሂደዋል፡፡

በሱሉስ ዝላይ ወንዶች አዲር ኑር ከመከላከያ አዲስ ክብረ ወሰን በመስበር ውድድሩን አሸንፏል፡፡

አዲር ኑር ባለፈው ዓመት በራሱ ተይዞ የነበረውን 15 ሜትር ከ33 ሴንቲሜትር ክብረ ወሰን ነው በዚህ ዓመት 15 ሜትር ከ79 ሴንቲሜትር በመዝለል ያሸሻለው፡፡

በዚህ ውድድር ብርሃኑ ሞዲሳ ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ደግሞ 15 ከ17 በመዝለል ሁለተኛ እንዲሁም ጌቱ ደቀባ ከፌደራል ማረሚያ 14.90 በመዝለል 3ኛ ወጥተዋል፡፡

በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች ፍፃሜ ደግሞ ዲራ ዲዳ ከኦሮሚያ ቀዳሚ ስትሆን፣ እታገኝ ወልዱ ከደ/ብርሃን ዩንቨርስቲ ሁለተኛ እንዲሁም ገበያነሽ አያሌው ከመከላከያ ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

በሴቶች ሱሉስ ዝላይ ዙርጋ ኡስማን ከሲዳማ ቡና 1ኛ፣ መሰረት ከበደ ከመከላከያ 2ኛ እንዲሁም ሰላማዊት ማሬ ከደ/ፖሊስ 3ኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡

ውድድሩ ዛሬ ከሰዓት ሲቀጥል ምሽት 11 ሰዓት በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች የሀገሪቱ የርቀቱ ኮከቦች ይፋጠጣሉ፡፡

ኢማና መርጊያ፣ ሙክታር እንድሪስ፣ አዱኛ ተገኝ፣ አባዲ አዲስ እና ሀጎስ በውድድሩ ተሳታፊ ከሚሆኑት መካከል ይገኙበታል፡፡

በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች 480ሺህ ብር የተመደበ ሲሆን፣ አጠቃላይ ለውድድሩ ማስኬጃ ደግሞ 1.6 ሚሊዮን ብር መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

ውድድሩ በመጪው እሁድ እንደሚጠናቀቅ የወጣው መርሃ ግብር ያስረዳል፡፡

በአዝመራው ሞሴ

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች