በሊጉ ኢትዮጵያ ቡናና አዳማ ከተማ ድል ቀናቸው

መጋቢት 4፣ 2009

በ18ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡናና አዳማ ከተማ ድል ቀናቸው፡፡

ወደ ጎንደር ተጉዞ ፋሲል ከነማን የገጠመው የኢትዮጵያ ቡና 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ ተመልሷል፡፡

ለቡና የማሸነፊያ ግቦቹን ያስቆጠሩት በ35ኛው ደቂቃ ኤሊያስ ማሞ፤ በ49ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሱናሚ፤ በ69ኛው ደቂቃ አስቻለው ማሞ እንዲሁም በ89ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም ናቸው፡፡

ለፋሲል ከነማ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ኤዶም ሆሶሮቪ በፍጹም ቅጣት ምት ነበር፡፡

ድሉን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና በ31 ነጥብ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል፡፡ ፋሲል ደግሞ በ26 ነጥብ ስድስተኛ  ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ወላይታ ዲቻን በማስተናገድ በ35ኛው ደቂቃ ሙጂብ ቃሲም ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ችሏል፡፡

በውጤቱም አዳማ ከተማ በ30 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች አዲስ አበባ ከተማ ከኢቲዮ ኤሌክትሪክ፤ ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና፤ አርባ ምንጭ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጅማ አባቡና በተመሳሳይ ውጤት ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል፡፡

የደረጃ ሰንጠረዡን ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ጨዋታ እየቀረው በ35 ነጥቦች ሲመራ ሲዳማ ቡና በ32፤ ኢትዮጵያ ቡናና ደደቢት በ31፤ አዳማ ከተማ ደግሞ በ30 ነጥቦች ከ2ኛ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

የሊጉን ከፍተኛ የግብ አግቢነትን ጌታነህ ከበደ ከደደቢት በ13 ግቦች ሲመራ አዳነህ ግርማ እና ሳላህዲን ሰዒድ በእኩል 9 ግቦች ይከተላሉ፡፡

Average (0 Votes)

ተያያዥ ዜናዎች ተያያዥ ዜናዎች