ኬንያ የስራ አጥነት ችግር ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ይበልጥ እየተገዳደራት ነው

መስከረም 02፣2010

ኬንያ  ከምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አጎራባች ሀገራት በምጣኔ ሀብት ከቀዳሚዎች ተርታ ብትሰለፍም በወጣቶች የስራ አጥነት እየተፈታተናት መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡ 

22 ነጥብ 2 በመቶ የደረሰው የኬንያ የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር እንደ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ኢትዮጵያ ከመሰሉ አጎራባች ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡

ባለፈው የአውሮፓዊያኑ  ዓመት መጨረሻ ላይ በታንዛኒያ የወጣቶች ስራ አጥነት 5 ነጥብ 2 ሲሆን የኡጋንዳ ደግሞ 4 በመቶ የደረሰ መሆኑን በቅርቡ የወጣው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰው ሀብት ልማት ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ በሩዋንዳና በብሩንዲ የነበረው የስራ አጥነት ምጣኔ በቅደም ተከተል 3 ነጥብ 3 በመቶ እና 3 ነጥብ 1 በመቶ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡

አሁን በኬንያ የተፈጠረው የስራ አጥነት ችግር የኢትዮጵያና የሩዋንዳ ተመሳሳይ ችግር ተዳምሮ የሚስተካከል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

በሀገሪቱ የተፈጠረው ስር የሰደደ የስራ አጥነት ችግር በቀጣይ ኬንያ በምስራቅ አፍሪካ ሊኖራት ላሰበችው የኢኮኖሚ የበላይነት ውጥን አሉታዊ ጥላ የሚጥልበት መሆኑን ተነግሯል፡፡

ይህም ችግር በቅርቡ በተካሄደው ግን በተሻረው የሀገሪቱ ምርጫ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሲያልፍ ፣ችግሩ በቀጣይ ድጋሜ በሚደረገው የሀገሪቱ የፕሬዝዳንት ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች መፎካከሪያ ርዕሰ ጉዳይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የስራ አጥነቱን ችግር ለመቅረፍም ሀገሪቱ በዝቅተኛ ወጪ የመሰረተ ልማት አቅርቦቱን ማስፋፋት እንደሚገባት የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ተናግረዋል፡፡

አሁን በኬንያ ለተፈጠረው ስር የሰደደ የስራ አጥነት ችግር በሀገሪቱ ካለው የህዝብ ቁጥር መሻቀብ ጋር እንደሚያያዝ ተመልክቷል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት ባወጣው መረጃ ከሆነ ሀገሪቱ 48.6 ሚሊዮን የሚጠጋ የህዝብ ቀጥር ያላት ሲሆን ይህም በአለም በህዝብ ቁጥር 29ኛ ደረጃ ላይ እንዳስቀመጣት ተነግሯል፡፡

ኬንያ በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር ያላት ቢሆንም በህዝብ ቁጥር እድገት ግን በቀጠናው ካሉ ሀገሮች ዝቅተኛ ሀገር ነች ተብሏል፡፡

ምንጭ፦ቢዝነስ ዴይሊ