ከወርቅ ምርት ተገቢው ጥቅም እየተገኘ አይደለም

ግንቦት 7፣ 2009

በአገሪቱ ህገ-ወጥ የወርቅ ንግድ መበራከት ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንዳይገኝ እያደረገው መሆኑን የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ ።

በሚኒስቴሩ የማዕድን ገበያ ትስስርና ትንበያ ዳይሬክተር አቶ ተወልደብረሃን አባይ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በባህላዊና ዘመናዊ መንገድ የተመረተ 6 ሺህ ኪሎግራም ወርቅ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ቢታቀድም የቀረበው ግን 1ሺህ 200 ኪሎ ግራም ብቻ ነው ።

በዚህም ማግኘት የተቻለው የውጭ ምንዛሪ 134 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዓለም አቀፍ ገበያ የወርቅ ዋጋ በመውደቁ በዘርፉ በህጋዊ መንገድ የተሰማሩ ባለሃብቶች ሳይቀሩ ምርቱን በህገ ወጥ መንገድ  ወደ ውጪ የሚያስወጡበት ሁኔታ መስፋፋት ለችግሩ ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል ።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮኘላን ማረፊያ በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሊወጣ የነበረ 15 ኪሎግራም ወርቅ መያዙን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

"በዘርፉ ለተሰማሩ ባህላዊ አምራቾችና ኩባንያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ንግዱ ህጋዊ መስመርን  እንዲከተል ለማድረግ እየተሰራ ነው " ብለዋል ።

በተጨማሪም በዘርፉ እየታየ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከህብረተሰቡና ከማዕድን ኢኒሼቲቪ ጋር በመተባበር ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ  እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

በወርቅ ገበያ የታየውን የዋጋ መቀነስ  ለማካካስ ታንታለም፣ የግንባታና ኢንዱስትሪ ነክና ሌሎች ማዕድናትን ወደ ውጪ ለመላክ እየተሰራ መሆኑን አቶ ተወልደብረሃን አስታውቀዋል ።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ አስተባባሪ ወይዘሮ ፍትህ ዓለሙ እንደገለፁት የአካባቢው ህብረተሰብ የተፈጥሮ ሀብቱን እንዲያለማ፣ እንዲጠብቅና በአግባቡ እንዲጠቀምበት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ ነው ።

ህብረተሰቡ በሀብቱ አያያዝና አጠቃቀም ላይ ግልፅ ግንዛቤ እንዲይዝ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው በራሱ የማህበረሰብ ሬዲዮ አሳታፊ የሆነ ፕሮግራም ቀርፆ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘለቀ ተሾመ ናቸው።