99 በመቶ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ግብር ከፍለዋል‑ ባለስልጣኑ

ነሐሴ11፣2009

በአዲሱ የቀን ገቢ ግምት መሰረት 99 በመቶ የሚሆኑት የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች የግብር ግዴታቸውን መወጣታቸውን የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በቀን ገቢ ግምቱ ላይ በቀረበው ቅሬታ ምክንያት ለ10 ቀናት ተራዘሞ የነበረው ግብርን አሳውቆ መክፈያ ጊዜ ትናንት ተጠናቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ  አስተዳደር ውስጥ  ካሉት 59 ሺህ 325 የደረጃ ‘ሐ' ግብር ከፋዮች 58 ሺህ 330 ግብር ከፋዮች የግብር ግዴታቸውን መወጣታቸውን የባለስልጣኑ የግብር ከፋዮች ትምህርት እና ኮሙዩኒኬሽን ም/ዳሬክተር አቶ ፋሲካ በላይ በስልክ ለኢቢሲ ገልጸዋል፡፡

በግመታው ሂደት ከቀረቡት አቤቱታዎች 42 በመቶ የሚሆኑት ማሻሻያ የተደረገላቸው  ሲሆን፣ 58 በመቶዎቹ ደግሞ እንደገና በማጥናት ምላሽ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል ኃላፊው፡፡

ማሻሻያ የተደረገላቸው አቤቱታዎች አብዛኞቹ የግብር ቅነሳ የተደረገላቸው እንደሆኑም ተመልክቷል፡፡ቀሬዎቹ ግን በጥናት ትክክለኛነታቸው የተረጋገጡት ናቸው ብሏል ባለስልጣኑ፡፡

በተሰጠው ተጨማሪ  ጊዜ የግብር ግዴታቸውን ያልተወጡ ግብር ከፋዮች በተቀመጠው ህግ መሰረት ቅጣትና ወለድ ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡

እስከ ነሓሴ 15 የደረጃ ‘ለ' ግብር ከፋዮችን ቅሬታ በመፍታትም ከአዲሱ ዓመት መግቢያ በፊት የደረጃ ‘ለ' ግብር ከፋዮችን ግብር ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ዳሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

በመላ አገሪቱ ዘንድሮ በተከናወነው የቀን ገቢ ግመታው በንግዱ ማህበረሰብ ቅሬታ ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ባለስልጣኑ ቅሬታ ላቀረቡ ወገኖች በአግባቡ ምላሽ መስጠቱን አመልክቷል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጭ ያሉ የ ‘ሐ'   ሆነ የ ‘ለ'  እና  ‘ሀ' ግብር ከፋዮች በየክልሎቹ ቀነ ገደብና አሰራር እየተፈፀመ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በአዝመራው ሞሴ