41 በመቶ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከግማሽ በላይ ውጤት አምጥተዋል-ኤጀንሲው

ሐምሌ 27 ፤2009

የ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በአገር አቀፍ ደረጃ ለፈተና ከቀረቡ ተማሪዎች ውስጥ 41 በመቶ የሚሆኑት ከ350 በላይ ማምጣታቸውን ሀገር ዓቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከአጠቃላይ ተፈታኞች 70 በመቶውን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን 49.1 ከመቶ የሚሆኑት የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ከ350 በላይ ውጤት ማምጣታቸውን የኤጀንሲው ምክትል ሃላፊ ዶ/ር ዘሪሁን ዱሬሳ አስታውቀዋል፡፡

በዘንድሮ የፈተና ውጤት ከአጠቃላይ ተፈታኞች ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች በተሻለ ውጤት ማምጣታቸውንም ዶ/ር ዘሪሁን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ፈተናውን ከወሰዱት መካከል 178 ሺህዎቹ የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ሲሆኑ የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞ ደግሞ 107,009 ተማሪዎች ናቸው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ለመፈተን መታወቂያ ከወሰዱት 288 ሺህ በላይ ተማሪዎች ውስጥ ፈተናውን የተፈተኑት 285,628 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናውን ተፈትነዋል፡፡

ኤጀንሲው በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የብሄራዊ ፈተና ውጤት የዩኒቨርስቲ መግቢያ መቁረጫ ውጤት ተለቋል በሚል የወጡ የተዛቡ መረጃዎች እንዳሉና ይህም በተፈታኝ ተማሪዎችና ወላጆች ዘንድ ውዝግብ እንዳይፈጥር አሳስቧል፡፡

ትክክለኛው ውጤት ነገ ከ8 ሰአት ጀምሮ በኤጀንሲው ድረ ገፅ www.neaea.gov.et ላይ በመከታተል ተአማኒነት ያለው መረጃ ልታገኙ እንደምትችሉ ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር፡- ናትናኤል ፀጋዬ