22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚያካሄዱት ውይይትና ድርድር ረቂቅ ደንብ ለማዘጋጀት ከስምምነት ላይ ደረሱ

የካቲት 8፣2009

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ እና 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚያካሄዱት ውይይትና ድርድር ረቂቅ ደንብ ለማዘጋጀት ከስምምነት ላይ ደረሱ፡፡

ፓርቲዎቹ ረቂቁን የሚያዘጋጅ ኮሚቴም አዋቅረዋል፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግን ጨምሮ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገሪቱን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማጠናከርና የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ ማስፋት አለማ ያደረገ ድርድርና ውይይት ለማካሄድ በሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ጥር10/2009 ዓ.ም መምከራቸው ይታወሳል።

በወቅቱም ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክርና ድርድሮቹ  የሚመሩበትን የስነስርዓት ማእቀፍ በተመለከተ የመነሻ ሀሳብ እንዲያቀርቡ  ከስምምነት ላይ በመድረስ ነበረ መድረኩ የተጠናቀቀው።

በዚህም መሰረት20 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይቱና ድርድሮቹን የሚመሩበት የስነስርዓት ማዕቀፍ መነሻ ሀሳብን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስገብተዋል።

በቀረቡ የመነሻ ሀሳቦች ላይም ፓርቲዎቹ ተወያይተዋል።

መነሻ ሀሳቡ የክርክርና ድርድር አካሄድ ስነስርዓትና የክርክሩ አላማ፣ የአመራር ሂደቱን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዲያ አጠቃቀምን ጨምሮ  አስራ ሁለት ነጥቦች አሉት።

አላማው በሚመለከት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በክርክርና በውይይት የሚነሱ ሀሳቦችን በግብአትነት በመውሰድ የሚሻሻሉ ሕጎች ካሉ መሻሻል የአፈጻጸም ጉለቶችን ማስተካከል የሚሉ ሀሳብ አቅርቧል።

የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ በበኩሉ የአገሪቱ ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ማስገኘት የክርክሩና የውይይቱ አላማ መሆን አለበት ብለዋል።

የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ችግር መለየትና መፍትሔ  እንዲገኝ ማስቻል የሚሉ ሀሳቦችም አካቷል።

ተሳታፊዎችን በሚመለከት ኢህአዴግን ጨምሮ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ፣ በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ፣ ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፍ ይችላሉ የሚል ሀሳብም ቀርቧል።

መድረክ ግን ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ በመሪ ተደራዳሪነት ሊቀርቡ ይገባል የሚል ሀሳብ አቅርቧል።

ፓርቲዎቹ በእነዚህና ሌሎች በቀረቡ የመነሻ ሀሳቦች ላይ  በዝግ ከመከሩ በሃላ  የቀረቡ ሀሳቦች በመሰብሰብ የጋራ  የድርድርና ክርክር ደንብ ለማርቀቅ ከስምምነት መድረሳቸውን በሰጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል።

ፓርቲዎቹ የድርድርና የክርክር መርሀ ግብሩ በፍጥነት እንዲጀመር በትኩረት ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸውንም አስታውቀዋል።

ሪፖርተር:- ሙባረክ መሀመድ