የአዲስ አበባ አስተዳደር 850 አውቶቢሶችን ሊገዛ ነው

ሰኔ 01፣2009

የአዲስ አበባን ትራንስፖርት ችግርን ለማቃለል 850 አውቶቡሶች ሊገዛ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ ለኢቢሲ እንደገለጹት የከተማ አስተዳደሩ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ 850 አውቶብሶችን ለመግዛት ከብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት አድርጓል።

አውቶቢሶቹ ወደ ስራ ሲገቡ ከ6 ሺህ ታክሲዎች ጋር የሚስተካካል አገልግሎት እንደሚሰጡ የገለጹት ዶ/ር ሰለሞን አውቶቢሶቹ በመዲናይቱ የተንሰራፋውን የትራንስፖርት ችግር ያቃልላሉ ብለዋል፡፡

ከጠቅላላ 850 አውቶቢሶች 100ዎቹ ለተማሪዎች አገልግሎት የሚዉሉ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ቀሪዎቹ ለነዋሪዎች ትራንስፖርት አገልግለሎት ይሰጣሉ  ተብሏል፡፡

ስምምነቱ ላይ ከተደረሱት አውቶቢሶች 50ዎቹ በአይነታቸው ለየት ያሉ ተነባባሪ አውቶቢሶች መሆናቸውን  የቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ሰለሞን ነግረዉናል፡፡

ቢሮው ባደረገው ጥናት መሰረት በከተማዋ ለሚኖረው  5 ሚሊዮን ህዝብ ገደማ  አምስት ሺህ ያህል አውቶቢሶች ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ሰለሞን ይህንኑ ለማሟላት ተጨማሪ 2 ሺህ 500 አውቶቢሶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከታማይቱ 1 ሺህ 500 ያህል አውቶቢሶች መኖራቸው ከበቢረሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

በአብዱልአዚዝ ዮሱፍ