ለ81 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞች የስራ እድል ማመቻቸቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት ገለጸ

የካቲት 02፣2009

ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው በአዲስ አበባ ለተደራጁ 81 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞች የስራ እድል ማመቻቸቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አቀፍ ኮንዶሚንየም ኤሌክትሪፌክሽን ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ጉሳዬ መንግስቴ እንደገለጹት የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው 81ዱ ኢንተርፕሪዞች በከተማው ኮንዶሚንየም ቤት ግንባታ በሚሰሩ የኤሌክትሪክ ስራ ላይ ይሰማራሉ።

የስራ ዕድል የተፈጠራላቸው የከተማው ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞች ወደ ስራ ከመሰማራቸው በፊት በቂ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው አስተዳደሩ በበጀት አመቱ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠርና ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ስራ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተፈጠረውን የስራ እድል ሌሎች ተቃማት በመከተል

ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠርና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ተወካይ ሳምሶን ነመራ እንደተናገረው የተፈጠረውን የስራ እድል በአግባቡ በመጠቀም ለሌሎች ወጣቶች አርአያ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ገልጿል።

የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር በሁለተኛው በጀት አመት ለ206ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ዘግቧል።