አሜሪካ ለአራት ሀገራት የ639 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ልትሰጥ ነው

ሃምሌ 02፤2009

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በድርቅና በእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት ለከፍትኛ የሰብዓዊ ቀውስ ለተጋለጡት ናይጄሪያ፤ የመን፤ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ የ639 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለመስጠት ቃል ገቡ፡፡

በዚህ እርዳታ ገንዘብም ለተጎጂዎች ሀገራት ህዝቦች አስቸኳይ ምግብ፤ ሰውነት ገንቢ ምግቦች፤ ህይወት አድን ህክምና፤ የንጽህና አገልግሎት፤ መጠለያና ከለላ ለመስጠት እንድሚያስችል ተገልጿል፡፡

የአሜሪካ አለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ በአራቱም ሀገራት ውስጥ የተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት ንጹሃን ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ እንዳያገኙ አድርጓል፡፡

አራቱ ሀገራት ማለትም ለናይጄሪያ 121 ሚሊዮን ዶላር፤ ለየመን እና ለደቡብ ሱዳን እያንዳንዳቸው 199 ሚሊዮን ዶላር፤ ለሶማሊያ 126 ሚሊዮን ዶላር ድርሻ እንደሚደርሳቸው ዩኤስኤይድ አስታውቋል፡፡

አሜሪካ በፈረንጆቹ 2017 ለእነዚህ ሀገራት ለመስጠት ያቀደችው የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ግቡን መቷል ማለት ነው፡፡

ይሁንና የአለም ምግብ ፕሮግራም ለሰብዓዊ መብት እርዳታ ያስፈልገኛል ከሚለው አጠቃላይ ገንዘብ ውስጥ አንድ ሶስተኛውን ብቻ እንደሚሸፍን ነው የተነገረው፡፡

ምንጭ፡ ቢዝነስ እስታንዳርድ