በኦሮሚያ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸው 450 አመራሮች መነሳታቸውን ክልሉ አስታወቀ

የካቲት 8፣2009

በኦሮሚያ ክልል እስከ ወረዳ ድረስ በተካሄዱ የመጀመሪያው ዙር የጥልቅ ተሀድሶ መድረኮች የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸው 450 የሚሆኑ አመራሮች በአዳዲስ መተካታቸውን ክልሉ አስታወቀ።

በመልካም አስተዳደር ችግር የተሰበሰበ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ሕገወጥ ገንዘብ በቁጥጥር ስር መዋሉም ተገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በክልሉ የአንደኛው ዙር የጥልቅ ተሀድሶ ንቅናቄ መድረክ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ

በክልሉ በተካሄዱ የመጀመሪያው ዙር የጥልቅ ተሀድሶ ንቅናቄ መድረኮች በክልሉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።

ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች እና አመራሮች በየደረጃው ሲያሳትፍ በቆየው መድረክ ለመልካም አስተዳደር እንቅፋት የነበሩ ችግሮችን መለየት እንደተቻለ ኃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ እስከ ወረዳ ድረስ የተካሄዱ የጥልቅ ተሀድሶ መድረኮች ተከትሎ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸው 450 የሚሆኑ አመራሮች በአዳዲስ መተካታቸውንም አቶ አዲሱ ተናግረዋል።

በመልካም አስተዳደር ችግር የተሰበሰበ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ሕገወጥ ገንዘብ በቁጥጥር ስር መዋሉንም አቶ አዲሱ አመልክተዋል።

የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ያላቸውን አመራሮች ወደ ሕግ በማቅረብ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ያሰባሰቡትን ንብረት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏልም ብለዋል።

በየደረጃው የሚስተዋሉ ችግሮችን አጣርቶ ለመለየት በአንደኛው ዙር የተሀድሶ እንቅስቃሴ የተጀመረው የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

ሪፖርተር:-መለሰ አምዴ