ቻይና በሙስና በተጠረጠሩ 440 ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ምርመራ እያደረገች ነው

ጥቅምት 9፣2010

ቻይና በሙስና በተጠረጠሩ 440 ከፍተኛ ባለስልጣኖቿ ላይ ምርመራ እያደረገች መሆኑን አስታወቀች፡፡

የቻይና የስነ ምግባር ጉዳዮች ባለስልጣናት በክልላዊ ደረጃና ከዚያ በላይ ሲሰሩ በነበሩ የላይኛው እርከን ባለስልጣናት ላይ ነው የሙስና ክስ  ማጣራት ሂደቱን እያካሄደች ያለው፡፡

ባለስልጣናቱ ባለፉት አምስት አመታት ፈፅመውታል በተባለ ሙስና ምርምራ እየተደረገባቸው መሆኑን የቻይና ባስልጣናት ገልፀዋል፡፡

እርምጃው የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ሙስናን ጠራርጎ ለማጥፋት የገባው ቃል አካል መሆኑን ተመልክቷል፡፡

ምርመራ እየተደረገባቸው ከሚገኙት 440 ባለስልጣናት መካከል 43ቱ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲው አባልና ተለዋጭ አባል ናቸው ተብሏል፡፡

ቻይና ከአምስት አመት በፊት በወሰደችው ተመሳሳይ እርምጃ 278 ሺህ የፓርቲው አባላትን መቅጣቷ የሚታወስ ነው፡፡

በሙስና ተጠርጥረው አገር ጥለው ከተሰደዱ 3453 ቻይናዊያን መካከል ከአለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት ኢንተርፖል ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር ለመዋል ክትትል እያደረገ መሆኑን ባለስልጣናቱ ገልፀዋል፡፡ እስካሁን ከ100 ከፍተኛ ባለስልጣናት 48 ያህል ተይዘው ወደ ቻይና ተመልሰዋል፡፡

የአሁኑ የፀረ ሙስና ዘመቻ የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ እያካሄደው ባለው 19ኛው ጉባኤ በሙሰኞች ላይ የማያወላዳ እርምጃ እንደሚወስድ መግለፁን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡

ፓርቲው ሙስና ከፊቱ የተደቀነ ከባድ ፈተና በመሆኑ በፅኑ ለመታገል መቁረጡን በጉባኤው መክፈቻ ላይ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሺ ዥን ፒንግ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ምንጭ፡‑ ሽንዋ