የሴት የመንግስት ሰራተኞችን የወሊድ ፈቃድ ከ3 ወደ 4 ወር ለማሣደግ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ፀደቀ

ህዳር 26፣2010

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴት የመንግስት ሰራተኞችን የወሊድ ፈቃድ ከ3 ወር ወደ 4 ወር ለማሣደግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ ባካሄደው 7ኛ መደበኛ ስብሰባ መልካም አስተዳደርን በማረጋገጥ ሂደት የመንግስት ሰራተኞችን ግዴታና ሀላፊነት እንዲሁም መብቶች ያስጠብቃል የተባለውን የፌዴራል መንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅን አፅድቋል፡፡

ምክር ቤቱ በተጨማሪ የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ በቀረበው ሪፖርትና የውሣኔ ሃሣብም ላይ ተወያያቶ አፅድቋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በህብረተሰብ ተሳትፎ ደንን ለማልማት ምቹ ሁኔታ እደሚፈጠርም ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግስትና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ለፍትሀዊ የመሠረታዊ አገልግሎቶች ማስፋፊያ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል 6ዐዐ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተጨማሪ ብድር ለማግኘት የተደረገውን ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅንም አፅድቋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግስትና በፈረንሣይ የልማት ድርጅት መካከል ለአዲስ አበባ ቄራዎች ቦታ ማዛወሪያና ማዘመኛ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የተደረገውን የ7ዐ ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅንም ምክር ቤቱ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ጂኦ-ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወያየት ለተጨማሪ ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

ሪፖርተር፡‑ ተሾመ ወልዴ