ፌደሬሽኑ ለህዳሴው ግድብ 3.2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

ግንቦት 08፣2009

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለታላቁ የህዳሴው ግድብ 3.2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

ፌደሬሽኑ ድጋፉን ያደረገው 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ስታዲዮም እየተካሄደ ባለበት ውቅት ነው፡፡

የፌደሬሽኑን ድጋፍ ፕሬዝዳንቱ ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ በስፍራው ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ የሚሆን የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን እና በዚሁ እንደሚቀጥልም ሻለቃ ሀይሌ ገልጿል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ሮማን ገ/ስላሴ በበኩላቸው ፌደሬሽኑ ለህዳሴው ግድብ ህዝባዊ መነቃቃትን እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ፌደሬሽኑ መሰል ተግባራቱን አጠናክሮ  እንዲቀጥል  በሃላፊዋ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በአዝመራው ሞሴ