ሁለት የብሪታንያ ኩባንያዎች ከገናሌ ዳዋ 250 ሜጋ ዋት የኤልክትሪክ ኃይል አመንጭተው ለመንግስት ሊሸጡ ነው

ጥር 29፣ 2009

ሁለት የብሪታንያ ኩባንያዎች ከገናሌ  ዳዋ 250 ሜጋ ዋት የኤልክትሪክ ኃይል አመንጭተው ለመንግስት ሊሸጡ ነው።

                          ፎቶ፥   ፋይል 

ኮንቲንጀንት ቴክኖሎጂና  ግሎቢክ የተሰኙት ኩባንያዎች የገናሌ  ዳዋ ቁጥር 6 የኤሌክትሪክ ኃይል  ማመንጫ ግንባታን ለማከናወን ባላቸው ፍላጎት ላይ ከፕሬዝዳንት ሙላቱ  ተሾመ ጋር ተወያይተዋል።

ኩባንያዎቹ  በኢትዮጵያ የግል ዘርፉ ሲገባበት የመጀመሪያ በሆነው የኃይል ማመንጫ  ግንባታ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲገቡ  የብሪታንያ  መንግስትም የ850 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደያዘላቸው ተናግረዋል።

የኩባንያዎቹ ዋና ስራ አስፈፃምሚ  አሌክስ ስቲዋር ለኢቢሲ  እንዳሉት የኃይል  ማምንጫ ፕሮጀክቱን በአምስት አመታት ወስጥ ገንብተው እንደሚያጠናቅቁ ገልፀዋል። 

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞንና በኢትዮጵያ ሶማሌ  ክልል ላይ  የሚገነባው  የገናሌ  ዳዋ የሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ  ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንደሚከናወን  ኩባንያዎቹ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ያድረጉትን ውይይት የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  የቢዝነስ ድፕሎማሲ  ተጠባባቂ  ዳይሬክተር  አርዓያ ገ/እጊዝያብሔር  ተናግረዋል።

መንግስትም ለፕሮጀክቱ  አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ፕሬዝዳንት ሙላቱ  መግለፃቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ከኃይል ማመንጨት ባሻገር 27 ሺህ ሄክታር መሬት የሚያለማ የመስኖ  ፕሮጀክትም የያዘ  ነው።

በዚህ በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነው የግል የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሚሰማሩት የብሪታንያ ኩባንያዎች  40 በመቶ የሚሆነውን የፕሮጀክቱን ግንባታ  ለኢትዮጵያዊያን ተቋራጮች  በንዑስ ተቃራጭነት እንዲሰሩ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ሪፖርተር ፥ ብሩክ ተስፋዬ