በ2050 የአይነስውራን ቁጥር በሶስት እጥፍ ሊያድግ ይችላል:-ጥናት

ሐምሌ 27፣2009

በሚቀጥሉት አራት አስርት አመታት በአለም ዙሪያ የሚገኙ አይነስውራን ቁጥር በሶስት እጥፍ ሊያድግ እንደሚችል ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡

በላንሴት ግሎባል ሄልዝ የሰፈረው ጽሑፍ እንዳመለከታው ህክምናው በተሻለ የገንዘብ ድጋፍ ካልታገዘ አሁን ያለው 36 ሚሊዮን  የአይነስውራን ቁጥር በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2050 ወደ 115 ሚሊዮን ሊያድግ ይችላል፡፡

በአይነስውርነት የሚጋለጠው የአለም ህዝብ በአማካይ እያሽቆለቆለ መሆኑን ያመለከተው ጥናቱ  እየጨመረ ያለው የህዝብ ቁጥርና የሰዎች አኗኗር በመሻሻሉ  በሚከሰት እርጅና ምክንያት ግን የአይነስውራን ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ አመልክቷል፡፡

ከ188 ሀገራት የተሰበሰበው መረጃ እንዳመለከተው ከ200 ሚሊዮን በላይ አይነስውራን እንዳሉ አመልክቷል፡፡ አሃዙ በ2050 ከ550 ሚሊዮን በላይ ሊያድግ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡

ደቡብ ምስራቅ ኤሲያ እንዲሁም ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት በከፊል በከፍተኛ መጠን የተጠቁ አከባቢዎች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

አይነስውርነትን ለመከላከል የቀዶ ህክምና እና ሰዎች የአይን መነጽር እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር ያስፈልጋል ብሏል ጥናቱ፡፡

በታዳጊ አገራት ውስጥ ያሉት የጤና ስርዓቶች መሻሻል፣ በርካታ የቀዶ ጥገና ባለሙያዎች እና ነርሶች ዘላቂ የዓይን ጤና እንክብካቤ እንዲሰጡ ማሰልጠን ያስፈልጋልም ተብላል፡፡

ደቡብ ኤስያ 11.7፣ ምስራቅ ኤስያ 6.2 ሚሊዮን፣ ደቡብ ምስራቅ ኤስያ 3.5 ሚሊዮን  እንዲሁም ከአጠቃላይ የህዝብ ብዛቱ ከ4 በመቶ በላይ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ ክፍል በከፍተኛ በአይነስውርነት የተጠቁ አከባቢዎች  መሆናቸው በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

የአይነስውርነት  ስርጭት በምእራብ አውሮፓ ደግሞ ከ0.5 ከመቶ በታች መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡

ምንጭ፤ ቢቢሲ