ትራኮማን ከአማራ ክልል ለማጥፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

ግንቦት 09፣2009

ላየንስ ካርተር ሳይት ፈረስት የተባለ ኢኒሼቲቭ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 ትራኮማ ከአማራ ክልል ለማጥፋት እየሰራ እንደሚገኝ ገለጸ።

የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የኢኒሼቲቩ ከፍተኛ አመራሮች በጽፈሕት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ላየንስ ካርተር ሳይት ፈረስት ኢኒሼቲቭ በሽታው በስፋት ከሚታይባቸው  የአለም  አከባቢዎች የአማራ ክልል ቀዳሚው መሆኑን ገልጿል።

ትራኮማን ከአማራ ክልል ብሎም ከአገሪቱ ለማጥፋት በሚያደርገው ጥረት የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ላየንስ ካርተር ሳይት ፈረስት ገልጿል ።

ኢኒሼቲቩ በሽታውን ለመከላከል በተደረገው ጥረት በአማራ ክልል ከአስራ አንድ ዓመታት በፊት በ31 በመቶ ወንዶች እና 69 በመቶ ሴቶች ላይ የነበረውን የትራኮማ  ስርጭት መቀነስ ተችሏል ብሏል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጿል።

ክለቡ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የላየንስ ክለብ አባል ሆነው ላደረጉት እንቅስቃሴ የክለቡ መስራች በሆነው በሚልቫን ጆንስ የተሰየመው የክለቡ  ከፍተኛ የእውቅና ሽልማት አበርክቶላቸዋል።

ኢኒሼቲቩ  ስራ ከጀመረበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2001 ጀምሮ  እስከ 2016 ዓ.ም በክልሉ አራት መቶ ሀያ ሺህ ለሚሆኑ  ሰዎች የአይን ቀዶ  ጥገና ሕክምና አድርጋል።

999 የአይን ቀዶ ጥገና ባለሞያዎችን ማሰልጠኑም ተገልጿል።

ኢኒሼቲቩ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በጋምቤላ ክልሎች የሚታየውን ፎካት የተባለ በሽታ  ለማጥፋት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።

ሪፖርተር:-ሙሉጌታ ተስፋይ