የአለም ኢኮኖሚ በ2017ና 2018 መጠነኛ እድገት ያስመዘግባል:- አይ.ኤም.ኤፍ

ጥቅምት 1፤2010

የአለም ኢኮኖሚ ማገገሙን ተከትሎ እ.ኤ.አ በ2017 እና 2018 መጠነኛ እድገት እንደሚመዘገብ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት/አይ.ኤም.ኤፍ/ ተነበየ፡፡

በአውሮፓ፣ ቻይና፣ ጃፓንና በአሜሪካ የታየው ሰፊ የኢኮኖሚ መነቃቃት ለትንበያው ተስፋ ሰጪ ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡

በዚህም እ.ኤ.አ በ2017ና 2018 የአለም ኢኮኖሚ በቅደም ተከተል በ3 ነጥብ 6 እና በ3 ነጥብ 7 በመቶ እንደሚያድግ በቅርቡ አይ.ኤም.ኤፍ ያወጣው የኢኮኖሚ ትንበያ መረጃ አመልክቷል፡፡

የአሁኑ ትንበያም ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ከወጣው ተመሳሳይ የትንበያ መረጃ ጋር ሲነፃፀር 0 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡

በአውሮፓ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ አሜሪካና በአዳጊ ሀገሮች የታየው ምጣኔ ሀብታዊ መነቃቃት የአለም ኢኮኖሚ በፍጥነት እያገገመ እንዲሄድ ምክንያት መሆኑን የአይኤምኤፍ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሞያ ሞሪስ ኦብስትፌልድ ተናግረዋል፡፡

የቻይና ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ በ2017 በ6 ነጥብ 8 በመቶ፤ በ2018 ደግሞ በ6 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚያድግ ተነግሯል፡፡ 

የአሜሪካ ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ በ2017ና በ2018 በቅደም ተከተል በ2 ነጥብ 2 በመቶና በ2 ነጥብ 3 በመቶ እንደሚያድግ አይ.ኤም.ኤፍ በትንበያው ጠቁሟል፡፡

የአውሮፓ ኢኮኖሚ በተያዘው ዓመት ማንሰራራት ሲያሳይ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ እንደሚያሽቆለቁል ተመልክቷል፡፡

እ.ኤ.አ በ2017 በ1 ነጥብ 5 በመቶ፤ በ2018 በ0.7 በመቶ እድገት ታስመዘግባለች የተባለችው ደግሞ በአለም ሶስተኛ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ጃፓን መሆኑዋን አይ.ኤም.ኤፍ በትንበያው ጠቅሷል፡፡

ምንጭ፦ ሽንዋ