በ2017 ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሀገራት የ2.4 በመቶ ኢኮኖሚ እድገት ያስመዘግባሉ፦አለም ባንክ

ጥቅምት 2፤2010

በዘንድሮ ዓመት ከሰዓራ በታች የሚገኙ ሀገራት የ2 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያስመዘግቡ አለም ባንክ ገለፀ፡፡

ከዚህ በፊት ተተንቢዮ የነበረው የ2 ነጥብ 6 የኢኮኖሚ እድገት ቢሆንም ደካማ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ምርታማነት ለእድገቱ መቀዛቀዝ ዋና ምክንያቶች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡

በተለይም የቀጠናውን ግማሽ ያህሉን የኢኮኖሚ እድገት የሚሸፍኑት ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ምጣኔ ሀብታቸው መዳከም ለአዝጋሚ እድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ነው የሚባለው፡፡

በያዝነው ዓመት በቀጠናው 2 ነጥብ 4 በመቶ እድገት የሚመዘገብ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2018 እና በ2019 እድገቱ ማንሰራራት በማሳየት በቅደም ተከተል 3 ነጥብ 2 በመቶና 3 ነጥብ 5 በመቶ ይመዘገባል ተብሏል፡፡

ናይጄሪያ የተፈጥሮ የነዳጅ ሀብት ቢኖራትም በያዝነው ዓመት 1 በመቶ አዝጋሚ እድገት እንደምታስመዘግብ ተጠቁሟል፡፡

ይህም ትንበያ ባለፈው ዓመት ከተተነበየው በ0 ነጥብ 2 በመቶ የቀነሰ መሆኑን ተመልክቷል፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሀገሪቱ የነዳጅ ማምረቻ መሰረተ ልማቶች ጥገና ላይ ያሉ በመሆናቸው ምርቱን በሚፈለገው መጠን ማምረት ባለመቻሉ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ዘንድሮ ከአንድ በመቶ በታች የኢኮኖሚ እድገት ስታስመዘግብ፤ እ.ኤ.አ በ2018 እና በ2019 በቅደም ተከተል 1 ነጥብ 1 በመቶና 1 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ይኖራታል ተብሏል፡፡

ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ የተዳከመ ኢኮኖሚያቸውን ዳግም ለማጠናከር ስርነቀል ለውጥ መተግበር እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ፦ሮይተርስ