በ2009 ከውጪ ንግድ 2 ነጥብ 91 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፦ንግድ ሚኒስቴር

መስከረም 19፣2010

በ2009 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከውጪ ንግድ 2 ነጥብ 91 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ገቢው ከ2008 በጀት ዓመት እቅድ ጋር ሲነፃፀር የ51 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡

በንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ በተለይ ለኢቢሲ እንደተናገሩት በ2009 በጀት ዓመት ሀገሪቱ ከውጪ ንግድ 2 ነጥብ 91 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች፡፡

በበጀት ዓመቱ ከውጭ ንግድ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም ከእቅዱ አኳያ የተመዘገበው ገቢ ሲታይ ግን የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ ሲያሳይ 61 በመቶ  የእቅዱ አፈፃፀም ደግሞ ተሳክቷል ብለዋል፡፡

የውጭ ገቢው አፈፃፀም የተዳከመውም በዋናነት በአለም አቀፍ ደረጃ የግብርና ምርቶች ፍላጎት መቀነሱን ተከትሎ የምርቶቹ ዋጋ ስላሽቆለቆለ እንደሆነም አቶ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በሰሊጥ ምርት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች የምርቱ አለም አቀፍ ፍላጎት ማነስ በመመልከት በሌሎች የሰብል ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ መገደዳቸውን ገልፀዋል፡፡

በተለይ ቡና፣ ቁም እንስሳት፣ ጥራጥሬ ሰብሎችና የወርቅ ምርቶች በህግ ወጥ ንግድ ወደ ውጪ አገራት መሄዳቸው ለውጭ ንግድ ገቢው መቀዛቀዝ ሌላው ምክንያት እንደሆነም ሀላፊው ጠቁመዋል፡፡ 

አምራች ኢንዱስትሪው እሴት የሚጨምሩ ምርቶችን በሚፈለገው ደረጃ ለውጭ ገቢያ አለማቅረብም በምክንያት ተጠቅሷል፡፡

ሪፖርተር፦ ሰለሞን አብርሃ