ኢትዮጵያ በ2009 ወደ ውጭ ለመላክ ካቀደችው የስጋ ምርት ግማሽ ያህሉን ብቻ ነው ያሳካችው

ሐምሌ 06፣2009

ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም ወደ ተለያዩ አገሮች ለመላክ ካቀደችው 38ሺህ 6 መቶ ቶን የስጋ ምርት ግማሽ ያህሉን ብቻ ማሳካቷን የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አህርሃም ተስፋዬ በተለይ ለኢቢሲ በስልክ  እንደተናገሩት  ወደ ውጭ ለመላክ የታቀደው የስጋ ምርት ያልተሳካው በተለያዩ ችግሮች ነው፡፡በተለይም በአገሪቱ ቆላማ የአርብቶ አደር አከባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ወደ ውጪ የሚላከው የስጋ ምርት በብዛትና በጥራት አለመገኘቱን በምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡

ከተፈጠረው ድርቅ በተጨማሪም ቄራዎች የወጪ ምርት በአግባቡ ያለማቅረብ፣ የገበያ ጥናታቸው ደካማ መሆንና ከአቅም በታች ማምረት እቅዱን በተፈለገው መጠን ለማሳካት እንዳላስቻለ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ተናግረዋል፡፡

እስከ በጀት አመቱ መጠናቀቂያ ድረስ ከእቅዱ ውስጥ 19ሺህ 779 ቶን ብቻ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የእቅዱን 50 በመቶ ብቻ ማሳካት መቻሉ ተመልክቷል፡፡

በዚህም  100.3 ሚሊዮን  ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማግኘት ተችሏል፡፡

አገሪቱ ወደ ሳውድ አረቢያ፣ዱባይ፣ባህሬን፣ኳታር እና ኦማን የስጋ ምርት በመላክ ለማግኘት አቅዳ የነበረው 146 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡

በ2009 ዓ.ም  በዘርፉ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍና በቀጣዩ ዓመት የስጋ ምርቱን በብዛትና በጥራት ወደ ውጪ አገሮች ለመላክ በአሁን ሰአት የከብቶች ማደለብያ ጣብያዎች እየተሰሩ መሆናቸውም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ ቄራዎች ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርቶች በአግባቡ እንዲያሟሉና የገበያ ጥናት  አድማሳቸውን በስፋት እንዲያካሄዱ በማድረግ እንዲሁም መንግስትም ቄራዎችን የመደገፍ ስራዎች እንደሚሰሩ ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡

በድርቤ መገርሳ