የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የ2017 የዓለማችን ምርጥ ፕሮጀክት ተባለ

ጥቅምት13 ፤2010

ኢንጂነሪንግ ኒውስ ሪኮርድ የተባለው አለም አቀፍ ተቋም የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን የአለማች የ2017 ምርጡ የማኑፋክቸሪግ ፕሮጀክት ብሎ ሰይሞታል፡፡

ፕሮጀክቶችን ሰርቶ ለማጠናቀቅ የፈጀው ጊዜ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ ያለው አስተዋጽኦ፣ የአከባቢ ብክለትን ለመቆጣጠር የተቀመጡ አሰራሮችና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለው ሚና የተቋሙ ምርጥ ፕሮጀክቶችን የሚመዝንበት መስፈርቶቹ ናቸው፡፡

ፓርኩ በአሁኑ ወቅት ለ10 ሺህ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ስራውን ሲጀምር ለ60 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች ኢትዮጵያውያንን በማሰልጠን ወደ ማምረትም ተሸጋግረዋል፡፡ ኤክስፖቱ ሙሉ ለሙሉ ሲጀመር ከሀዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ በቀን እስከ 50 ኮንቴነር ምርት ወደ ውጭ ይላካል፡፡

የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ አለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው 17 የአሜሪካ፣ የሲሪላንካ፣ ሆንግ ኮንግ፣ የህንድና ቻይና ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ያሉበት ፓርክ ነው፡፡

ፓርኩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕክል ለመሆን ላስቀመጠችው ግብ ስኬታማነት ፈር ቀዳጅ መሆኑ ይነገርለታል፡፡

በ300 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የሃዋሳ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ፓርክ በ250 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ነው የተገነባው፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚመረት ምርት ሙሉ በሙሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሲሆን በአመት አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡

መቀመጫውን አሜሪካ ያደረው ኢንጂነሪንግ ኒውስ ሪኮርድ በአለማችን በየጊዜው የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን በ20 ዘርፎች እያወዳደረ ይሸልማል፡፡  

ምንጭ፡- ኢንጂነሪንግ ኒውስ ሪኮርድ