የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የ2009 ዕቅድ አፈፃፀሙን አፀደቀ

ነሐሴ 12፣2009

የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የ2009 ዕቅድ አፈፃፀሙን አፀድቋል፡፡

በዓመቱ በተለያዩ  ክልሎች የመስክ ምልከታ በማድረግ  ጥሩ ስራ ተሰርቷል ተብሏል፡፡

የፓርቲዎች የእርስ በርስ  ግንኙነት  ለማጠናከርም የመስክ ጉብኝቱ አስተዋፅኦ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

በመገናኛ ብዙሃን ክርክር ለማድረግ የታሰበው እቅድ አለመፈፀም መደበኛ ስብሰባውን በተቀመጠው መርሃ ግብር አለማካሄደ ደግሞ ጉድለቶች ተብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ በ2010 ዕቅድ ላይም ውይይት ያደረገ ሲሆን በ2009 ያልተፈፀሙ እቅዶችን በትኩረት ለመስራት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በዋና ዋና አገራዊ ፖሊሲዎች ላይ ውይይት በማካሄድ ግብዓት ለመንግስት ማቅረብ፣በአካባቢና ማሟያ ምርጫ ላይ በስፋት መሳተፍ የዕቅዱ አካል ሁኗል፡፡

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የአምስት ፓርቲዎች አባልነት ጥያቄንም ተመልክቶ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ከአምስቱ ፓርቲዎች  ውስጥ የተሟላ መረጃ ያቀረቡትን የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት ፣እና የመላ ኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ብቻ በመሆናቸው የአባልነት ጥያቄውን ተቀብሏል፡፡

ሌሎቹ ፓርቲች መረጃቸውን ያሟሉ ፓርቲዎችና የምክር ቤቱ አባል መሆን የሚፈልጉ ፓርቲዎች የአባልነት መመዘኛውን አሟልተው አባል መሆን እንደሚችሉም ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡

ሪፖርተር፡‑ ጌቱ ላቀው