የ16 ዓመት የሶሪያ ታዳጊ የ2017 አለም አቀፍ የህፃናት የሰላም ሽልማትን አሸነፈ

ህዳር 26 ፣2010

አንድ የ16 ዓመት የሶሪያ ታዳጊ የ2017 አለም አቀፍ የህፃናት የሰላም ሽልማትን አሸነፈ፡፡

 ሽልማቱ የተበረከተለት መሐመድ አል ጁንድ  የሶሪያ ስደተኛ ህፃናትን መብት እንዲረጋገጥ ጥረት ስላደረገ እንደሆነም ተነግሯል፡፡ 

7 ዓመት በዘለቀው የሶሪያ ጦርነት ስደተኛ በመሆን ተጠቂ የሆነው አል ጁንድ ከቤተሰቡ ጋር በመሆን በሊባኖስ በሚገኝ የሶሪያ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ለ200 ህፃናት ትምህርት እየሰጠ ይገኛል ተብሏል፡፡

መሐመድ አል ጃኡድ ሽልማቱ የተበረከተለት በህፃናት መብት ዙሪያ በሰራችው መልካም ስራዎች የ2014 የኖቤል ሽልማት ከተሰጣት ከፓኪስታኗ ተወላጅ ማላላ ዮሱፍ እጅ ነው፡፡

በዚሁ ወቅት አል ጃኡድ ትምህርት ቤት ፊደል መቁጠሪያ ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች ማንነታቸውን የሚያውቁበት፣ ጓደኛ የሚያፈሩበት፣ የራሳቸውን ትዝታ የሚያኖሩበትና በነፃነት ሀሳባቸውን የሚያንፀባርቁበት ቦታ ነው ብሏል፡፡ 

የሶሪያ መፃኢ ተስፋ  በህፃናት ላይ የተመሰረተ መሆኑንና የህፃናቱም የወደፊት እጣ ፈንታ በትምህርት ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመገንዘብ መሐመድ አል ጁንድና ቤተሰቦቹ  ለስደተኞች ህፃናት ድጋፍ ማድረጋቸውን የኖቤል ሽልማት አሸናፊዋ ማላላ ዮሱፍ  አድንቃለች፡፡

ታዳጊው ሞሃመድ ጁንድ የትምህርትና እንክብካቤ ሽልማት ከማግኘቱ ባሻገር እሱ የጀመረውን ስራ ከዳር ለማድረስ የሚረዳ የ100ሺህ ዩሮ ፕሮጀክት ወስዷል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ 28 ሚሊዮን ህፃናት ለስደት እንደተዳረጉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከዚህም ውስጥ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህፃናት ስደተኞች በሶሪያ ግጭት የተፈናቀሉ ናቸው ተብሏል፡፡

ሽልማቱን በየዓመቱ ኪድስ ራይት የተባለ አለም አቀፍ ድርጅት በህፃናት መብት መሻሻል ዙሪያ ለውጥ ላመጡ ታዳጊ ህፃናት ያበረክታል፡፡

ምንጭ፦ ሽንዋ