በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም እስካሁን 159ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል

ህዳር 28፣2010

በድርቤ መገርሳ

በ2009 በጀት ዓመት በተጀመረው የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር በክልል ዋና ከተሞች እና በሁለት የከተማ መስተዳድሮች እስካአሁን 159ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

           ፎቶ  ፡ የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ

በፕሮግራሙ በተለያዩ የከተማ ልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡  ተጠቃሚዎቹም  በከተማ ግብርና በአረንጓዴ ልማት፣በከተማ ፅዳትና ውበት፣በመሰረተ ልማት እና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ላይ  በመሳተፍ በሚያገኙት ገቢ የምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አቦዘነች ነጋሽ  ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በተደራራቢ የአካል ጉዳት፣ በዕድሜ እና በጤና ምክንያት በስራ ላይ መሰማራት የማይችሉ 30 ሺ 4 መቶ የሚሆኑ ዜጎች የቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ ከድህነት ወለል በታች ያሉ የከተማ ነዋሪዎች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ከማስቻል ባሻገር፣ በሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱም ተናግረዋል፡፡

መርሃ ግብሩ በቤተሰብ ደረጃ የሚተገበር ሲሆን በአማካይ በመርሃ ግብሩ በታቀፈው ሰው ልክ አንድ የቤተሰብ አባል በወር ከ1ሺ 3 መቶ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኝ ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

በዚህ አግባብ በአንደኛ ዙር የተመለመሉት ተጠቃሚዎች እስከ 5 አመት ድረስ እንደሚታቀፉ ተገልጿል፡፡   

በቀጣይ ዓመታትም ፕሮግራሙ ወደ ሌሎች ከተሞች እየሰፋ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡በሁለተኛው ዙር ተጨማሪ ተጠቃሚ የሚሆኑ ከተሞች በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ፣ ደሴ፣ አዳማ፣ ጂግጂጋ፣ሃዋሳ እና ድሬዳዋ መሆናቸውን የገለፀው ኤጀንሲው፣ በ2010 በጀት አመት ሩብ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተመልክቷል፡፡

በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በአቅም ግንባታ፣ በኑሮ ማሻሻያ፣ በማህበረሰብ አቀፍ የልማት ስራዎችና በማህበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክቶች ከ4.7 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን ለማቀፍ መታቀዱን ኤጀንሲው ገልጿል፡፡

የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከአለም ባንክ በተገኘ 300 ሚሊዮን ዶላር ድግፍና መንግስት በተጨማሪ በመደበው 150 ሚሊዮን ዶላር እየተተገበረ ያለ መርሃ ግብር ነው፡፡