በዓመት 150 ሺህ ህፃናት በተላላፊ ባክቴሪያ በመጠቃት ህይወታቸውን ያጣሉ፦ ጥናት

ጥቅምት 28፣2010

በታዳጊ ሀገራት ከእናት ወደ ህፃናት በሚተላለፍ ባክቴሪያ በዓመት 150 ሺህ ህፃናት ህይወታቸውን እንደሚያጡ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

በቸልታ እየታየ የመጣው ይህ ተላላፊ በሽታ የተወለዱ ጨቅላ ህፃናትን ህይወት ከመቅጠፍ ባለፈ በጽንስ ላይ ህፃናትን እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት እንደሚያስከትል በብሪታኒያ የሚገኙ የዘርፉ ተማራማሪዎች ተናግረዋል፡፡

በአለማችን ከ5 እናቶች አንዷ "Group B Streptococcus" በተሰኘ የባክቴሪያ ዝርያ የሚጠቁ ሲሆን በሽታውም የጽንስ መቋረጥ እንዲፈጠር ከማድረግ ባለፈ በህፃናት ላይ የአይን መጥፋትና መስማት ያለመቻል የመሰሉ ቋሚ የአካል ጉድለቶች እንደሚያመጣ ተነግሯል፡፡ 

አፍሪካ 13 በመቶ የሚሆነውን የአለም ህዝብ የያዘች ቢሆንም በበሽታው ተጠቂ በመሆን ግን የአለማችንን 65 በመቶ ድርሻ ትይዛለች ተብሏል፡፡

እንደ ጥናቱ ከሆነ በበሽታው ምክንያት የሚከሰት አብዛኛው ሞት መከላከል የሚቻል ሲሆን ይህንንም ለማሳካት ለባክቴሪያው ክትባት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተመልክቷል፡፡

ከአለም በአፍሪካ በተላላፊ ባክቴሪያ (ኢንፌክሽን) የሚጠቁ እናቶች ቁጥር በአመዛኙ ከፍተኛ ቢሆንም የዚህ ችግር ምንጭ ምን እንደሆነ በውል አይታወቅም ነው የሚባለው፡፡

በእርጉዝ እናቶች ላይ በተላላፊ ባክቴሪያ (ልክፈት)  የሚከሰት በሽታን ለመከላከል በሙከራ ላይ ያለው ክትባት 80 በመቶ የተሳካ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን በዓመት የ231 ሺህ ጨቅላ ህፃናትና እናቶች ህይወት ይታደጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

በፍጥነት መጠናቀቅ እንዳለበት የተነገረለት ይህ ክትባት እውን ሲሆንም ከየትኛውም አህጉር በበለጠ ለአፍሪካ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ምንጭ፦ ሲጂቲኤን