በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ1ሚሊየን 720 ሺህ በላይ ዶላር ተያዘ

ጥቅምት 13፣2010

ከአዲስ አበባ ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ1ሚሊየን ሰባት መቶ ሃያ ሺህ ዶላር በላይ  ተይዞ ለመንግስት ገቢ  ሆነ።

ዶላሩ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ግብረ ሀይል በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን በተመሳሳይ 32 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በገቢዎችና ጉምሩክ ሰራተኞች መያዙን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የላከልን መረጃ ያመለክታል።

ከአሜሪካን ዶላር በተጨማሪ የሌሎች ሀገራት መገበያያ ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

የጅግጅጋ ገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የህግ ማስከበር ጉዳዮች ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ መሀመድ እንደተናገሩት በህገ ወጥ መንገድ በህዝብ ማመላለሽ መኪና ተጭኖ ከአዲስ አበባ ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ወቻሌ ከተማ ሊገባ ከነበረ ዶላር በተጨማሪ  ከፍተኛ መጠን ያላቸው የሳውዲ ሪያል፣የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣የኳታር የመገበያያ ገንዘቦች በቦሞባሶ ከተማ በፌደራል ፖሊስ የኮንትሮባንድ ንግድ መከላከያ ግብረ ሃይል አባላት ተይዟል፡፡

በህገ ወጥ ስራው የተሳተፉ አካላት ጉዳይ በህግ እየተጣራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ምክትል ስራአስኪያጁ በሃገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰውን ህገ ወጥ ንግድና የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሣትፎ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡ ዘገባው የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዬች ቢሮ ነው፡፡