የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ የግል ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር 100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊሰጥ ነው

ጥቅምት 2፤2010

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ የግል ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር 100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደረግ አስታወቀ፡፡

‹‹ሴፍውስ ግሮውዝ ካፒታል ፈንድ›› በተባለ ሀገር በቀል የግል ድርጅት በኩል ፈሰስ የሚደረገው ገንዘብ በሀገሪቷ የሚገኙ የግል ኩባንያዎች ተስፋፍተውና ተጠናክረው ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው ተብሏል፡፡

ድጋፉም ሀገሪቷ የወጠነችው ቁልፍ ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሳኩና እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው እንደሚያግዝ የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት አምብሮስ ፋዮል ተናግረዋል፡፡

በሁለት ኢትዮጵያዊያን የተቋቋመው ‹‹ሴፍውስ ግሮውዝ ካፒታል ፈንድ›› በአምራች ኢንዱስትሪ፣ ግብርና፣ በፍጆታ ዕቃዎች እና በተቀነባበሩ የግብርና ምርቶች ላይ የተሰማሩ የግል ኩባንያዎችን ለማጠናከር በገንዘብና በእውቀት እገዛ ያደርጋል ተብሏል፡፡

በዚህም ፈንዱ በእያንዳንዱ ኩባንያ ከ3 እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር መዋለንዋያ ያፈሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡    

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በግሉ ዘርፍ ይህን ዓይነቱን ድጋፍ ሲያደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

በቀጣይም ኢንዱስሪ ፓርክ፣ ታዳሽ ሀይልና ሞባይል ባንክ ላይ ባንኩ ድጋፍ ለማድረግ የወሰናቸው የትኩረት መስኮች ናቸው ተብሏል፡፡

ባለፉት 5 ዓመታት ባንኩ በአፍሪካ ያለውን ኢንቨስትመንት ለማጠናከር 10 ቢሊዮን ዮሮ የሚሆን ገንዘብ ድጋፍ ሰጥቷል ነው የሚባለው፡፡  

ምንጭ፦ ሲኤንቢሲ