ተመድ ለደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቀውስ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገለጸ

ግንቦት 8፣ 2009

በደቡብ ሱዳን በተከተሰተው የስደተኞች ቀውስ የምግብ፤ ውሃና ጤና አገልግሎቶች አቅርቦትን ለማሟላት ቢያንስ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተመድ ይፋ አድርጓል፡፡

የተመድ ስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ እንደገለጹት ከሆነ በአገሪቱ መራር የእርስ በእርስ ጦርነት አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ መከሰቱ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው በከፍተኛ ቁጥር እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡

ደቡብ ሱዳን የስደተኞች ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ከአለም ቀዳሚ ስትሆን እስከ አሁንም ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናዉያን ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የምስራቅና መካከኛ አፍሪካ አገራትን መዳረሻቸው ማድረጋቸውን ድርጅቱ አብራርቷል፡፡

ድርቅ እና ረሃብ መከሰት ደግሞ ሁኔታውን በከፍተኛ ሁኔታ ማባባሱን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም እርዳታ ለጋሾች የተጠየቀውን ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የእርዳታ ገንዘብ በአስቸኳይ እንዲለግሱ ተመድ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ምንጭ፡ ተመድ