በደቡብ አፍሪካ ሊስቴሪያ በሚባል ባክቴሪያ 36 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

ህዳር 26፣2010

በደቡብ አፍሪካ ሊስቴሪያ በሚባል በሽታ ቢያንስ 36 የሚሆኑ ሰዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሊስቴሪያ   በምግብ መመረዝ ምክንያት  የሚፈጠር  ሞኖሳይቶጂነስስ  የሚባል  የባክቴሪያ  ዓይነት ሲሆን  ባክቴሪያው በደም ዝውውር አማካይነት በመራባት የተለያዩ ሰውነት ክፍሎችን ላይ መርዝ በማመንጨት  ሰውን  ሊጎዳ  የሚችል  አስከፊ በሽታ  መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች  ይገልፃሉ፡፡

በተለይም በነፍሰጡርና በወላድ እንዲሁም በህፃናት ላይ በሽታ የመከላከል አቅምን በማዳከም የማጥቃት እድሉ ከፍ ያለ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በደቡብ አፍሪካ በምእራባዊ ኬፕታወን እና በከዋዙሉ ናታል 557 የሚሆኑ ሰዎች በዚህ በሽታ መያዛቸው   ተዘግቧል፡፡

የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር  ሞጾአሌዲ በአከባቢው የተፈጠረውን የሊስቴሪያ  በሽታ በፀረ ተዋሲያን መድኃኒት ማከም እንደሚቻል  ተናግረዋል፡፡

የሊስቴሪያ  ባክቴሪያ በአፈር፣በውሃ እና በአትክልት ላይ አንደሚገኝ  እና የእንስሳት ተዋጽኦና  የአትክልት  ምርቶችን  ሊመርዝ ይችላል፡፡   

የደቡብ አፍሪካ መንግስት  ሊስቴሪያን  ለመከላከል እጅ መታጠብ  እጅግ አስፈላጊ መሆኑን  እየመከረ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡