የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 46 በመቶ አድጓል-የዱባይ ንግድ ምክር ቤት

ጥቅምት 13 ፤2010

የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እአአ በ2016 ወደ 46 በመቶ ማደጉን የዱባይ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ያስጠናው ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት መጠኑ ወደ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ማደጉም ተገልጿል፡፡

በጥናቱ መሰረት የአገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ዕድገት ያሳየው በመሰረተ ልማትና የአምራች ዘርፎች ባሳዩት ከፍተኛ መነቃቃት ምክንያት ነው፡፡

በምስራቅ አፍሪካ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ የመሪነቱን ቦታ የያዘች ሲሆን ሞሪሸስና ማዳጋስካርም በዘርፉ የተረጋጋ ፍሰት እንዳላቸውም ተጠቁሟል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ በአጠቃላይ አገራዊ ምርት ማሽቆልቆል ቢታይም ኢትዮጵያ እአአ በ2016 10.9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበች ሲሆን ሴኔጋል 6.6 በመቶ እንዲሁም ኬንያና ሩዋንዳ 6 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግበዋል፡፡ 

ጋና በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት በ3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን የኢንቨስትመንት ፍሰቷ 9 በመቶ በማደግ 3.5 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ፍሰት አስመዝግቧል፡፡

የጋና ተረጋጋ ፍሰት በነዳጅና ጋዝ ዘርፍ የተደገፈ ሲሆን የቀጠናው የካካዋ ማቀነባበር ኢንዱትሪም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

ከሰሀራ በታች ባሉ አገራት ወደ ውጭ የሚላከው ምርት ከአጠቃላይ ምርቱ 78.7 በመቶውን እንደሚሸፈን ዘገባው ያስረዳል፡፡    

ምንጭ፡- ፋይናንሻል ትሪቡን