‹‹ቴሌራዲዮሎጂ›› የተባለ ህክምና በ60 የሀገሪቱ ሆስፒታሎች ሊጀመር ነው

ሐምሌ 5፣2009

በኮምፒውተር ስርዓት የተነሳ የሰዎች ውስጣዊ ምስል መረጃ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማስተላለፍ የሚረዳ ‹‹ቴሌራዲዮሎጂ›› የተባለ ህክምና በ60 የሀገሪቱ ሆስፒታሎች እንደሚጀመር ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከ3 ሳምንት በሃላ የህክምና ቴክኖሎጂው እንደሚጀመር የተነገረለት ይህ ቴክኖሎጂ ለታካሚዎቹ የተሻለ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡

በዚህም በጨረርና በሌሎች የህክምና ቴክኖሎጂዎች የሚታከሙ ታካሚዎች የውስጣዊ አካላቸው ምስል ሌላ ቦታ ባለ ባለሞያ ታይቶ ህክምና እንዲያገኙ ይረዳል ነው የተባለው፡፡

በዚህም ታካሚው ሳይጉላላ ባለበት ቦታ ሆኖ ስለህመሙ መረጃ እንዲያገኝ ይረዳ ተብሏል፡፡  

የህክምናው አገልግሎቱ በሚጀመርባቸው ሆስፒታሎችም አስፈላጊ ግብዓት ከተሟላላቸው ከ7 የህክምና ማዕከላት ጋር እንደሚተሳሰሩም ነው የተመለከተው፡፡

በዚህም ታካሚው በቅርቡ ካለ የጤና ተቋም የዘርፉን ህክምና በኮምፒውተር የመረጃ መረብ እንዲያገኝ እድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡ 

በቀጣይም በሀገሪቱ ያሉ ሆስፒታሎች የህክምና አገልግሎቱን ለማግኘት ከቅዱስ ፓውሎስ፣ ጥቁር አንበሳ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ጅማ፣ ሀሮማያ ዩኒቨርስቲና አይደር ሆስፒታሎች ጋር በኮምፒውተር መረብ እንዲተሳሰሩ እንደሚደረግም ተጠቁሟል፡፡ 

የህክምና መድሀኒቶች መረጃ በኮምፒውተር መረብ ለማስተላለፍ በ3 ሺህ 500 የጤና ተቋማት መካከል በኮምፒውተር መረብ ለማስተሳሰር ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር እየተሰራ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ቴሌራዲዮሎጂ በጨረርና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች የሚገኝ የሰዎች ውስጣዊ ምስል በዘርፉ ባለሞያ የሚተረጎመው መስሉ በተመረተበት ቦታ ሳይገኝ ሌላ ቦታ ሆኖ ነው፡፡   

ቴሌሜዲሲን ደግሞ ቅርብ ቦታ ለማይገኙ ታማሚዎች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ህክምና አገልግሎት መስጠት ማለት ነው፡፡

ምንጭ፦ኢቢሲ