በመጪው ክረምት ከ16 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በበጎ አድርጎት ስራ ይሳተፋሉ፦ ሚኒስቴሩ

ግንቦት 08፣2009

በመጪው ክረምት በወጣቶች የበጎ አድርጎት ስራ ከ16 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በመላ አገሪቱ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ናስር ለገሰ በተለይ ለኢቢሲ እንደገለጹት የወጣቶች የበጎ አድርጎት ስራ ወጣቶች በእረፍት ጊዜያቸው እንደየአቅማቸው ህብረተሰቡን የሚያገለግሉበት ተግባር ነው፡፡

በዚህም ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቻቸው ከሚመለሱ የዮኒቨርስቲ ተማሪዎች በተጨማሪ ከተለያዮ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ተማሪዎች በአካባቢያቸው እንደየአቅማቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡ 

ወጣቶቹ ከሚሳተፉባቸው ስራዎች መካከል የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የመንገድ ትራፊክ፣  ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ደም ልገሳ፣ አካባቢ ጥበቃና ውበት፣ የጤና አጠባበቅ ትምህርት፣ ችግኝ ተከላና አቅመ ደካሞችን መንከባከብ ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡

ወጣቶች በበጎ አድራጎት ተግባር ሲሰማሩ ስራቸው ተገቢ እውቅና አግኝቶ ከትምህርት ልምዳቸው ጋር እንዲያያዝ የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

ይህም ወጣቶች በዘርፉ ለመሰማራት ጥሩ መነሳሳት ይፈጥርላቸዋል ሲሉ ሃላፊው ነግረውናል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበጎ አድርጎት ስራውን ለማስፈፀም የእቅድ ዝግጅት ስራ እያከናወነ ነው ያሉት አቶ ናስር፤ በዘርፉ ስራም ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የማስተባበር ሚና ይወጣል ብለዋል፡፡

በመጪው ክረምት በወጣቶች የበጎ አድርጎት ስራ ከ16 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በመላ ሀገሪቱ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል አቶ ናሲር፡፡

ወጣቶች በክረምት ወራት እራሳቸውን ካአልባሌ ቦታ አርቀው ትርፍ ጊዜያቸውን ህብረተሰቡን በሚጠቅሙ በጎ ተግባራት ላይ እንዲያሰማሩም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በሰለሞን አብርሃ