ሲጋራ ማጨስ ከ10 ሞት ውስጥ የአንዱ ምክንያት መሆኑ በጥናት ተረጋገጠ

መጋቢት 28፣ 2009

ጤናን በማቃወስ የሰውን ልጅ ለሞት ከሚያበቁ ጎጂ የሱስ አይነቶች ውስጥ በዋናነት ተጠቃሽ የሆነው ሲጋራ በአለም ላይ በተለያየ ምክንያት ከሚከሰት 10 ሞት የአንዱ ምክንያት እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል፡፡

ሲጋራን ማጨስ በአለም ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ያሳሰባቸው ተመራማሪዎች በ195 አገራት ላይ ተመስርተው በሰሩት ጥናት ነው የሲጋራ ማጨስ ልማድ የሚያስከትለውን የሞት መጠን ማረጋገጥ የቻሉት፡፡

ከአለም አገራት በሲጋራ ማጨስ ልምድ ምክንያት ከሚሞቱት ግማሽ ያክሉ በ4 አገራት ብቻ እንደሆኑ ጥናቱ ያመለከተ ሲሆን አገራቱ ቻይና፣ ህንድ፣ አሜሪካና ሩሲያ ናቸው፡፡

ለበርካታ አመታት የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ የተለያዩ ፖሊሲዎች ተግባር ላይ ቢውሉም የአለም ህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር መጨመሩ ግን ለአጫሾች ቁጥር መጨመር ዋነኛው ምክንያት ሆኗል፡፡

አሁንም የሲጋራ አምራቾች አዳዲስ የገበያ አማራጮችን በተለይም በታዳጊ አገራት ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ማምረታቸውን ከቀጠሉ በሲጋራ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያደገ እንደሚሄድ ጥናቱ ያብራራል፡፡

ሲጋራን ማጨስ ያለጊዜ ሞትና አካል ጉዳትን በማስከተል በ2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ የጤና ጠንቅ ሲሆን በትንባሆ አምራቾች ላይ ጠንከር ያለ ቁጥጥርና እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ ጉዳቱ እያደገ ይቀጥላል ተብሏል፡፡

ጥናቱ እ.ኤ.አ ከ1995 እስከ 2015 ባሉት 25 ዓመታት የጊዜ ገደብ ውስጥ በ195 አገሮች የተሰራ ነው፡፡

በ2015 ዓመት ብቻ 1 ቢሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በየቀኑ ሲጋራ ያጨሱ ሲሆን ከነሱ መካከል 1 አራተኛ ወንዶች፤ 1 ሃያኛው ደግሞ ሴቶች እንደሆኑም ተረጋግጧል፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ