ህወሓት 42ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የሚያከረው ችግሮችን ለመፍታት ቃል በመግባት መሆኑን አስታወቀ

የካቲት 10፣2009

ህወሓት የተመሰረተበት 42ኛ ዓመት በዓሉን የሚያከብረው ድርጅቱ በጥልቅ ተሀድሶ የለያቸውን ችግሮች ለመፍታት ቃል በመግባት መሆኑን አስታወቀ።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ የተመሰረተበትን 42ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባወጣው መግለጫ የካቲት 11 የትግራይ ህዝብ ከግፍና መክራ ለመላቀቅ የነጻነት ችቦ የተለኮሰባት ቀን ናት ብሏል።

የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ ህወሓት መላ የአገሪቱን ህዝቦች ባሳተፈው ትግል የልማት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲ ድሎች ተገኝቷል ብሏል።

በአገሪቱ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ባለፉት አስራ አምስት አመታት በተደረገው ሰፊ ርብርብ የህዳሴ ጉዞ መበሰሩንም የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ አብራርቷል።

ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በገጠርና ከተማ የሚኖረው ህዝብ በልማታዊ እና ዴሞክራሲያዊ መስመር ከድርጅቱ ጎን ተሰልፎ በመረባረቡ በርካታ የልማት፣ የዴሞክራሲ ድሎች እያስመዘገበ መምጣቱን ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው አስታውሷል።

የዘንድሮ የካቲት 11 የሚከበረውም ከባለፉት ዓመታት የህዳሴ ጉዞ ተሞክሮ በመውሰድ ድርጅቱ በጥልቅት በማደስ ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ራሱን በገመገመበት ወቅት ነው ብሏል።

ለጦርነት አውድማ ይውሉ የነበሩ ተራሮች እና ሜዳዎች አሁን በአረንጋዴ ልማት ለመሽፈን በገጠር አከባቢ የተጀመረው የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ዘመቻ መልሶ ማልማት ብቻ ሳይሆን የመስኖ ልማት አቅምን በማሳደግ ረገድም ትልቅ ፋይዳ ማበርከቱን መግለጫው አብራርቷል።

በከተሞችም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወጣቶችን በማደራጀት እና የስራ እድል በመፍጠር የተጀመሩት እንቅስቃሴዎች አበራታች መሆናቸውንም መግለጫው ጠቅሷል።

በማሕበራዊ ልማት ዘርፎች በተለይ በትምህርትና ጤና ተደራሽነት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የገለጸው መግጫው በጥራት በኩል የሚታዩ ችግሮች የማስተካከል ሂደትም በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን አመልክቷል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው የድርጅቱን ወቅታዊ ሁኔታ ሲገመግም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት በጉልህ መንጸባረቁ፣ ለፍትህ ብሎ ትልቅ መስዋእትነት የከፈለው ህዝብ የመልካም አስተዳደር አገልግሎት በበቂ ሁኔታ አለማግኘቱን አረጋግጧል። በአመራሩ የህዝባዊነትና አገልጋይነት ባህሪ እየተሸረሸረ መምጣቱ፣ ስልጣን የግል መጠቀሚያ ማድረግ አስተሳሰብ መኖሩን ገምግሟል።

በድርጅቱ ጸረ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ፣ የመከባበርና የመቻቻል ባህሪ መቀዛቀዝ እና የተለመደውን ዴሞክራሲያዊ ትግል እየፈዘዘ መምጣቱንም ለይቷል።

ድርጅቱ ያጋጠመውን ችግር ከታሪክ በመማር የሚታወቅበትን የመተጋገል ባህሪና የውስጥ ችግሮች የመፍታት ልምድ በመመልስ በተያዘው የህዳሴ ጉዞም ለመድገም እንዲሁም የጸረ ድህነት ትግሉ ለማቀጣጠል ይተጋል ብሏል ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው።

አንድነቷ የጠነከረ፣ ሰላሟ የተረጋገጠ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመፍጠር ሁሉም የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መስዋእትነት ከፍለዋል ያለው መግለጫው አልፎ አልፎ በትግራይ ህዝብና በሌላው ህዝብ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር የሚጥሩ ሀይሎች መኖራቸውንና ድርጅቱ ከትግራይ ህዝብና መላ ኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም እንደሚታገላቸው አስታውቋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ጎን በመቆም ላደረገው የዓመታት መራር ትግልና ለከፈለው ክቡር መስዋእትነት አክብሮቱንና ምስጋናውን ይገልጻል ብሏል መግለጫው።

የብሔሮችና ብሔረሰቦች እኩልነት ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያረጋገጠች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በጋራ ለአንድ አላማ ለታገሉት አጋር እና እህት ድርጅቶችም ማዕከላዊ ኮሚቴው ያለው ክብርና መስጋና ገልጿል።

ሁሉም ብሔሮችና ብሄረሰቦችና ህዝቦች በከፈሉት ክቡር መስዋእትነት የእኩልነት፣ የመከባበርና የመፈቃቀር ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ተችሏል ያለው መግለጫው አሁን የተያያዘችውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል ህወሓት/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጎን በመቆም ጠንክሮ እንደሚሰራ አረጋግጧል።