በአንበሳ የከተማ አውቶብስ ዲፖ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 46 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ

የካቲት 05፣  2009

በአንበሳ የከተማ አውቶብስ  አገልግሎት ድርጅት በመከኒሳ  ቅርንጫፍ ዲፖ  ላይ በደረ የእሳት አደጋ 46 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ።

ዛሬ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀሞ  አካባቢ  በሚገኘው የድርጅቱ ጋራዥ ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ  ለጥገና የገቡ ግምታቸው 18 ሚሊዮን የሚጠጋ  11 አውቶብሶች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።

በአንበሳ የከተማ አውቶብስ  አገልግሎት ድርጅት የመከኒሳ ቅርንጫፍ   ዲፖ  ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ  ሳሙኤል ገ/ኪዳን በተለይ ለኢቢሲ  እንዳሉት ምክንያቱ  ባልታወቀ ሁኔታ የተነሳው የእሳት አደጋ ለመለስተኛ ጥገና  ጋራዥ የገቡትን አውቶብሶች፣የመለዋወጫ ዕቃዎች ማከማቻና ጋራዡን ሙሉ ለሙሉ አውድሞታል።    

በእሳት አደጋው 46 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ  አደጋው መንስኤ በሚመለከታቸው አካላት ማጣራት  እየተድረገበት ነው ብለዋል።

እስከሁን  ባለው መረጃ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ።  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መካላከልና መቆጣጠር ኤጀንሲ ሰራተኞች በአደጋው ቦታ  ደርሰው እሳቱ ሊጠፋ ችሏል።

በጋራዡና መለዋወጫ ዕቃ ማከማቻ ላይ የደረሰው ጉዳት በትራንስፖርት ስምሪቱ ላይ መስተጋጎል  እንዳይፈጥር  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ በአስቸኳይ ጋራዡ መልሶ እንዲቋቋም እንደሚያደርግ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ተናግረዋል።

ሪፖርተር ፥  ብሩክ ተስፋዬ