ባለስልጣኑ በየወቅቱ የሚታዩ የሚዲያ ዘገባዎች ህጉ በሚፈቅደው አሰራር እንዲያስፈፅም ም/ቤቱ ጠየቀ

ህዳር 28፣2010

የብሮድካስት ባለስልጣን በየወቅቱ የሚታዩ የሚዲያ ዘገባ አዝማሚያዎችን ህጉ በሚፈቅደው አሰራር መከታተል እንደሚገባው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የባለስልጣኑን የ2010 በጀት አመት ዕቅድና የሩብ አመት አፈጻጸሙን ገምግሟል፡፡

ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርታቸውን ያቀረቡት የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶም ባለስልጣኑ ከዲጂታል ቴሌቪዥን ሽግግር አንፃር የተሰጠውን ተልዕኮ እያከናወነ መሆኑና ለሽግግሩ የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎች ማዘጋጀቱንም ገልፀዋል፡፡

በበጀት አመቱ የመገናኛ ብዙሃን ከማስፋፋት አንፃር የመገናኛ ብዙሃን ምዝገባና ፍቃድ መስጠት፣ የሬዲዮ ሞገድ ማሻሻያና ምዝገባ እንዲሁም የብሮድካስት ሚዲያ የቴክኒክ ብቃትን ለማረጋገጥ ባለስልጣኑ ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡

ሪፖርቱን መሰረት በማድረግ ለባለስልጣኑ ግብረ መልስ የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ከባለስልጣኑ ፍቃድ ሳያወጡ በሳተላይት አማካኝነት በሃገር ውስጥ ቋንቋ ከውጭ ሃገር የሚያሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ያሉባቸውን ችግሮች ፈተው ወደ መደበኛ የህግ አሰራር እንዲገቡ ከማድረግ አንፃር ባለስልጣኑ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የዲጂታል ቴሌቪዥን ሽግግርን የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎች በሚመለከተው አካል ቀርበው ይፀድቁ ዘንድ በባለስልጣኑ የተደረገው ጥረት በጥንካሬ የተመለከተው ቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጁ ረቂቆች ለማፅደቅ ባለስልጣኑ  በህግ ማዕቀፎቹ ተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን  ማከናወን  እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

ሪፖርተር፡‑ ተስፉ ወልደገብርኤል