እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ እንድትሆን አሜሪካ እውቅና መስጠቷ የአለም መሪዎችን አስቆጥቷል

ህዳር 28፣2010

እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ እንድትሆን  አሜሪካ እውቅና  መስጠቷን  የአለም መሪዎች አውግዘዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት በቴሌቭዥን ቀርበው አገራቸው እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና እድትሆን እውቅና መስጠቷ መናገራቸውን ተከትሎ ነው በአረብ አገራትና በሌሎች የአለም አገራት መሪዎች ዘንድ ውሳኔው እየተወገዘ ያለው፡፡

መሪዎቹ አሜሪካ ያሳለፈችው ውሳኔ የመካከለኛው ምስራቅን ብቻ ሳይሆን የአለምን ሰላም የሚያናጋ ነው ብለዋል፡፡

የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ  ለውሳኔው  ፈፅሞ እውቅና እንደማይሰጡ ገልፀው፣ ከእንግዲህ በኃላ አሜሪካ የእስራኤልና የፍልስጤም የሰላም ሸምጋይ ሆና መቅረብ አትችልም ብለዋል፡፡ውሳኔው እንዲያውም የእስራኤልን ወራራ በይፋ ማበረታታት እንደሆነ ነው የምንቆጥረው ብለዋል፡፡በዚህም የፍልስጤም መሪዎች የአሜሪካን ውሳኔ ተከትሎ ሶስት  የቁጣ ቀናትን አውጀዋል፡፡

የአሜሪካን ውሳኔ በይፋ ተቃውመው ካወገዙ የአለም አገራት መካከል ሊባኖሱና ዮርዳኖስ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ ውሳኔው በአረብና በሙስሊም አገራት ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን የሚፈጥርና የሰለም ሂደቱን የሚጎዳ ብለውታል፡፡

ሳኡዲ አረቢያ የአሜሪካን ውሳኔ ተቀባይነት የሌለውና ኃላፊነት የጎደለው ስትል አጣጥለዋለች፡፡

ኳታር በበኩሏ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ውሳኔ ሰላም እየሻቱ ባሉ ወገኖች ላይ የሞት ውሳኔ ከማሳለፍ የሚቆጠር ነው ብለዋል፡፡

የፈንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማርኮን በበኩላቸው ፈረንሳይ ለውሳኔው እውቅና እንደማትሰጥና የፍልስጤምና እስራኤል የሁለትዮሽ መፍትሄን አገራቸው እንደማትደግፍ አመልክተዋል፡፡

ጀርመን ፣ቱርክና ፓኪስታንም ውሳኔው ለቀጠናውና ለአለም ሰላም የማይበጅ በመሆኑ ተቀባይነት የለው ነው ብለዋል፡፡

ከተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት 15 አባል አገራት ውስጥ  ስምንት ያህሉ በጉዳዩ ላይ እንዲመከርበት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራም ጠይቀዋል፡፡

በአንፃሩ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአሜሪካ ውሳኔ የእስራኤል ታሪካዊ የድል ቀን ነው ብለዋል፡፡

እስራኤል እ.ኤ.አ 1967 ከአረብ አገራት ጋር በገባችው  ጦርነት የምስራቅ እየሩሳሌምን በኃይል  ከያዘች ወዲህ  የወደፊት መናገሻዬ ትሆነኛለች ብላ በሰላም ድርድር ላይ ላለችው ፍልስጤም መራር ውሳኔ ነው፡፡በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር እውቅና የሌለው የእየሩሳሌም የእስራኤል መዲናነት አሁን ላይ አሜሪካ ደጋፊ ሆና መቅረቧ በቀጠናው ላይ ከባድ ወቅት መምጣቱን አመላካች ነው ይላሉ የዘርፉ ተንታኞች፡፡

ምስራቅ እየሩሳሌም ሙስሊሞች እንደ 3ኛ ቅዱስ ቦታቸው የሚቆጥሩት የአል አቅሷ መስጊድ መገኘት እና አይሁዶችም የ3ሺህ ዓመት ታሪክ ያለው ቅዱስ ስፍራቸው አድርገው በመቁጠራቸው ፍትጊያው የሰፋ እንዲሆን አድርጎታልም ተብሏል፡፡

ምንጭ፡‑ አልጀዚራና ቢቢሲ