የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት እንዲሰራ ተጠየቀ

ህዳር 27፣2010

ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት እንዲሰራ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴዉ ኮሚሽኑ ለህብረተሰቡ ግልጽ መረጃ መስጠት እንዳለበትም ገልጿል፡፡

የኮሚሽኑን የ2010 እቅድና የ1ኛ ሩብ አመት አፈፃፀም  ሲገመግም በተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ለተረጂነት ለተዳረጉ ዜጎች በተለይም ለሴቶችና ህፃናት  የተደረገዉን ድጋፍ በበጎ ጎኑ አንስቷል፡፡

ለአደጋ ስጋት የሆኑ አካባቢዎችን  በመለየት መረጃዉን ለሚመለከታቸዉ አካላት ማስተላለፉንም  በተሻለ አፈፃፀም ተመልክቷል፡፡

ኮሚሽኑ የሚያስተዳድረዉ ከፍተኛ  ሀብት ከኪራይ ሰብሳቢነት  በፀዳ መልኩ  ጥቅም ላይ እንዲዉል  መስራት እንደሚገባዉም  ቋሚ ኮሚቴዉ አሳስቧል፡፡

የኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸዉ በጥናት ለተለዩና በድርቅ ምክንያት ለተረጂነት ለተዳረጉ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች  የእለት ደራሽ እርዳታ እየቀረበላቸዉ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች  አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች  በተከሰተዉ ግጭት ምክንያት  ለተፈናቀሉ ዜጎችም  ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

መንግስት በሩብ አመቱ  ለአደጋ ምላሽ ስራዎች 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር  ወጪ ማድረጉ ተገልፀል፡፡

ዘገባዉ የሪፖርተራችን ተሾመ ወልዴ ነዉ፡፡