ደቡብ ሱዳን በዋና ከተማዋ ጁባ የደህንነት መቆጣጠሪያ መሳሪያ መጠቀም ጀመረች

ህዳር 26 ፣2010

ደቡብ ሱዳን በዋና ከተማዋ  ጁባ ወንጀልን ለመቆጣጠር የሚያስችል የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራና ድሮውን ጥቅም ላይ ማዋሏን አስታውቃለች፡፡

የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት እንደገለጹት  የደህንነት ሁኔታን ለማጠናከር የሚያስችል የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራ (ሲሲቲቪ)እና የአየር ላይ የድሮውን ቅኝት መጀመራቸውን አስታውቀዋል᎓᎓

የፕሮጀክቱ   ሥራ አስኪያጅ  ክፊር ሺልደር  እንደገለጹት  በጁባ   11 የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎች  እንደተተከሉና በሁለት ድሮኖች የአየር ላይ ቅኝት እንደሚያደርጉ  ነው የተናገሩት᎓᎓

" በአደባባይ  የሚዘርፉ  ሰዎች ከአሁን  በኋላ  ወንጀል መፈጸም አይችሉም  ከሰሩት ጥፋት ማምለጥ ስለማይችሉ ቅጣታቸውን ያገኛሉ " የፕሮጀክቱ ኃላፊ፡፡

ደቡብ ሱዳን  በታህሳስ  2013   በተከሰተው የስልጣን ሽኩቻ   ወደ ማያበራ የእርስ በርስ ጦርነት ገብታለች᎓᎓ሳልቫ ኪር  ሪክ ማቻርን  ስልጣኔን ሊነጥቅ ነው በሚል ከነበሩበት ሃላፊነት በማንሳታቸው፣ ሪክ ማቻር ደግሞ ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ለማስወገድ አማጺዎችን አደራጅተው መዋጋት ከጀመሩ አራት አመት ሆኗቸዋል፡፡

ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሲገድል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያንን  ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል᎓᎓ በያዝነው አመት የተባበሩት መንግስታት  ድርጅት የአፍሪካ ታላቁን የስደተኛ ቀውስ በማስተናገድ ከሶሪያ እና ከአፍጋኒስታን  ቀጥላ ደቡብ ሱዳን በ3ተኛነት ደረጃ አስቀምጧታል᎓᎓

ምንጭ፡‑ ሲጂቲኤን