የቀድሞው የየመኑ ፕሬዝዳንት አሊ አብዱላህ ሳላህ መገደላቸው እየተነገረ ነው

ህዳር 25፣2010

የቀድሞው የየመን ፕሬዝዳንት አሊ አብዱላህ ሳላህ  መገደላቸውን በሁቲ አማፂያን ስር ያሉ መገናኛ ብዙሃን እየገለፁ ነው፡፡

ሁቲዎች በመሰረቱት መንግስት ውስጥ በአገር ግዛት ሚኒስቴር ስር የሚተዳደር አንድ ሬድዮ የቀድሞው የየመን ፕሬዝዳንት መገደላቸውን ወሬ ይዞ መውጣቱን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

እንደዘገባው ከሆነ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተገደለ የተባለውን የየመን የቀድሞ መሪ  የሚመስል  ተንቀሳቃሽ ምስል ታጣቂዎች መኪና ላይ ሲጭኑ የሚያሳይ በስፋት ሲሰራጭ  ተስተውሏል፡፡

ይሁን እንጂ አስክሬኑም ይሁኑ አሊ አብዱላህ ሳላህ ስለመገደላቸው የፀና ማረጋጋጫ አለማግኘታቸውን ቢቢሲና አልጀዚራ ዘግበዋል፡፡

አልጀዚራ ከቅርብ ምንጭ አገኘሁት ባለው መረጃ አሊ አብዱላህ ሳላህ ብቻ ሳይሆን የእርሳቸው ዋና የደህንነት ሹማቸው ሁሴን አል ሀሚድምም ተገድለዋል፡፡

አብዱላህ ሳላህ ፓርቲ መሪያቸው ተገድሏል ስለሚለው ዜና ማስተባቢያ ቢሰጡም ፣እስከ አሁን ግን በህይወት ስለመኖራቸው በአደባባይ መታየት አለመቻላቸውን ዜናውን የበለጠ ለጥርጣሬ በር እንዲከፍት አድርጎታል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የየመኑ ፕሬዝዳንት  አሊ አብዱላህ ሳላህ ከሁቲዎች ጋር አለመስማማት ውስጥ ከገቡ ወዲህ ጦራቸው ከሁቲ ታጣቂዎች ጋር ሲዋጋ መሰንበቱን የአልጀዚራ ዘገባ አመልክቷል፡፡

እናም ሁቲዎች የአብዱላህ ሳላህ ወታደሮች ይዘውት የነበረውን የሰነዓ አብዛኛውን ቦታ መቆጣጠራቸውን አልጀዚራ አረጋግጧል፡፡

አሊ አብዱላህ ሳላህ የመንን ለረጅም ጊዜ ሲመሩ ቆይተው ከስልጣን የወረዱት እ.ኤ.አ በ2011 በተነሳባቸው ህዝባዊ አብዮት  ነበር፡፡