ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች የሚገኘው ደም አገራዊ ፍላጎቱን እየሸፈነ አይደለም ፡ ብሄራዊ የደም ባንክ

ህዳር 25፣2010

ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች የሚገኘው የደም መጠን የአገሪቱን ፍላጎት የሚያረካ አለመሆኑን የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ኤጄንሲ አስታወቀ።

ብሔራዊ የደም ባንኩ እንደገለጸው በተያዘው ሩብ አመት 12,300 የደም ዩኒት ተሰብስቧል። ይህም ከእቅዱ ስልሳ ከመቶ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን አሁን ላይ ያለውን አመታዊ የሆስፒታሎች የደም ፍላጎት ለማርካት የደም ለጋሾች ቁጥር ማሳደግ ያስፈልጋል ተብሏል።

በብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች አገልግሎት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ዶክተር ተመስገን አበጀ ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም የአገሪቱን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ የሚያረካ የደም አቅርቦት ላይ ለመድረስ ግን ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል᎓᎓

የአለም የጤና ድርጅት የሚጠይቀው ቢያንስ ከዜጎች አንድ ከመቶ የሚሆን ደም መሰብሰብ አለበት የሚለውን መስፈርት እንዳላሟላም ጠቁመዋል።

አብዛኞቹ የአገራችን ትልልቅ ከተሞች ከቤተሰብ ምትክ ወጥተው ከበጎ ፈቃደኞች ወደ ተገኘ ደም መግባታቸውን የገለጹት ዶክተር ተመስገን በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ከተሞች ግን ደም የመለገስ ባህል አልዳበረም ብለዋል።

በአገሪቱ የጤና ተቋማት በየቦታው መስፋፋት፤ ትላልቅ ሆስፒታሎች መገንባት፤ የኩላሊት ንቅለ ተከላን የመሳሰሉ ብዙ ደም የሚጠይቁ ህክምናዎች በአገር ውስጥ መሰጠት መጀመራቸው የደም ፍላጎት እንዲጨምር እያደረጉት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ደም ከለጋሾች በነጻ ይሰበባል፤  ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎችም በነጻ ይሰጣል ያሉት ተጠባባቂ ዳይሬክተሩ ያም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ፍላጎትና አቅርቦት ይጣጣማል  ማለት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

በተለይ ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮች ሲመጡ የደም እጥረት  እንደሚያጋጥም ነው ያለከቱት᎓᎓

እንዲህም ሆኖ ግን ከበጎ ፈቃደኞች በሚለገስ ደም የእናቶችና ህጻናት ሞትን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡

በ1962 ዓ.ም የተቋቋመው ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት በቂና ደህንነቱን የጠበቀ ደም ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ሁሉ የማድረስ ተልእኮን አንግቦ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል᎓᎓

በብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ኤጄንሲ ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው አቶ አለማየሁ ደምሴ ደም ሲለግሱ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ገልጸው ደም በመለገስ የሚመጣ ጉዳት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ደም መለገስ  ወገንን መርዳት ስለሆነ ሁላችንን ልንተገብረው ይገባልም ብለዋል፡፡

ሌላው ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው አቶ ወልደሚካኤልም ደም መለገስ የሌላውን ህይወት ለማትረፍ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ በየጊዜው እየመጣሁ ደም እለግሳለሁ ብለዋል᎓᎓

ከብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ኤጄንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2009 ዓ.ም 173 ሺህ ዩኒት ደም ተለግሷል። በያዝነው 2010 ዓ.ም ደግሞ 240 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዷል᎓᎓ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ 25 የደም ባንኮች እንዳሉም ተመልክቷል።

በመስፍን ገብረማርያም