የቻይናው ኩባንያ የአፍሪካ ቅርንጫፉን በአዲስ አበባ ከፈተ

ህዳር 13 ፣2010

የቻይና ሸንዝሄን ኦትቦንድ አሊያንስ የአፍሪካ ቅርንጫፉን በአዲስ አበባ  ከፍቷል᎓᎓

በቻይናዋ ሼንዝሄን ከተማ መሰረቱ ያደረገው ሸንዝሄን ኦትቦንድ አሊያንስ በአፍሪካ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለማመቻቸት ቅርንጫፉ በአዲስ አበባ መክፈቱን ገልጿል።

ሸንዝሄን ኦትቦንድ አሊያንስ የሼንዝሄን ኩባንያዎች በውጪ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ በትብብር እንዲሰሩ ለመርዳት የተቋቋመ  መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው᎓᎓

በቢሮው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የሸንዝሄን ኦትቦንድ አሊያንስ ምክትል ሊቀመንበር ሱን ቲያንሉ እንዳሉት የከተማይቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በአውሮፓውያኑ  2017  302 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር  እንደሚደርስ ይጠበቃል᎓᎓

ገቢ የሚገኘው ከከፍተኛ  ቴክኖሎጂ ምርቶች መሆኑን ገልጸው ከተማይቱም ይህንን ውጤታማነቷን ለሌሎች ሃገራት ማካፈል ትፈልጋለች ብለዋል᎓᎓

የቻይናዋ ሼንዝሄን  ከተማ ዜድቲኢ /ZTE/፣ ሁዋዌ  እና ሺንዝሄን ኢነርጂ ግሩፕን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ትታወቃለች᎓᎓

በከተማይቱ ታዋቂነት ያላቸው ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መገኘታቸው በቻይና "ሲሊከን ቫሊ"የሚል  ቅጽል ስም አሰጥቷታል᎓᎓

በመገናኛና  ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ  ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሀነ ቀለታ የሸንዝሄን ከተማ   ኩባንያዎች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአፍሪካ ለሚኖራቸው  እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ምርጫቸው አድርገዋል ብለዋል።

አቶ ብርሃነ ኢትዮጵያ እንደ  ሁዋዌ እና ዜድ ቲ ኢ በመሳሰሉ ኩባንያዎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ   አገልግሎት ተጠቃሚ ሆናለች ብለዋል᎓᎓ ሌሎች የሼንዝሄን ኩባንያዎችም ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በትብብር እንዲሰሩ  ጥሪ አቅርበዋል᎓᎓

የኢትዮጵያ  መንግስት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎትን ለማሳደግ በ250 ሚሊዮን ዶለር ወጪ በአዲስ አበባ የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ  እየገነባ መሆኑን ሽንዋ በዘገባው አመልክቷል።